የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

AMN-መስከረም 24/2017ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ፣ የከፍተኛ ባለሞያዎች ኮሚቴ ያካሄደውን የኢትዮጵያ የዓመቱ የብሪክስ ተሳትፎ ግምገማ፣ ኢትዮጵያ ስለተሳተፈችባቸው ሁለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባዎች እና የብሪክስ ሴክሬታሪያት ሪፖርቶች በስብሰባው ላይ ቀርበዋል።

እንዲሁም በጥቅምት ወር በሩሲያ ስለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ዝግጅትን የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ ማሞ ምህረቱ የብሪክስ ማዕቀፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ተጨማሪ ከፍተኛ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከሆነች ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ የማዕቀፉ መድረኮች ላይ በንቃት መሳተፏን አቶ ማሞ አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የብሪክስ የኢትዮጵያ ምክትል አስተባባሪ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ዲፕሎማሲያችንን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።

የቅንጅት ኮሚቴው አባላት በቀጣይ ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጉልህ ሚና እንድትጫወት በትብብር በንቃት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በቀጣይም ይህን መድረክ በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በዲፕሎማሲው መስክ በንቃት ተሳትፎ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኮሚቴው የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ የመጨረሻ ቅርጽ ላይ መስማማቱም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የአመቱ የብሪክስ ተሳትፎ ከገመገመ በኋል ቀጣይ ተሳፎን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያ ሚና እና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ሀሳቦችን ለይቷል።

በጥቅምት ወር የሩሲያ ከተማ በሆነችው ካዛን ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ዝግጅት ከየኮሚቴው አባልት የሚጠበቁ ሥራዎችን መለያታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review