የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር የፌዴራል ስርዓቱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር የፌዴራል ስርዓቱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው

AMN – ህዳር 2/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር መቀራረብን በመፍጠር የፌዴራል ስርዓቱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር ሲሆን፤ በመሪ ሃሳቡ ላይ የትንተና መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባኤዎችና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት፤ ባለፉት 18 ዓመታት በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስተናጋጅነት ሲከበር ቆይቷል።

ይህም ሕዝቦች ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያጎለብቱ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያፀኑ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በሕገ-መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችም የተሰሩበትና ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና አንድነታቸውንና ሰላማቸውን በጋራ እንዲያጸኑ፣ መሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፍፃሜ እንዲደርስ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በኩል የጎላ ሚና ነበረውም ብለዋል።

ዘንድሮ የሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በሚደረግ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ተናግረዋል።

ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ያለ ሀገራዊ መግባባት አይፀናም ያሉት አፈ-ጉባኤው ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ-ብሔራዊ አንድነት መሰረት መሆኑንም አንስተዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያን ብዝኀ ማንነት ዕውቅና ከመስጠት በላይ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነትና ሰላምን ለማፅናት አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የፌዴራል ስርዓቱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባትና በየጊዜው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመነጋገርና በመመካከር በመፍታት ኀብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሚና ያለው ነውም ብለዋል።

በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች በየደረጃው የሚከበር መሆኑን አንስተው፤ ከህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review