AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹንና አገልግሎቱን በማስፋት የባሌ ሮቤ ዋቆ ጉቱ ኤርፖርት ተርሚናልን አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው የባሌ ዞን ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ይህ የዋቆ ጉቱ ኤርፖርት ተርሚናል የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳለጥ ከሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ በተጨማሪ ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ባሌ ሮቤ ዋቆ ጉቱ ኤርፖርት 14 ሳምንታዊ በረራዎችን እንደሚያደርግ ገልጿል።