AMN ህዳር 21/2017 ዓ .ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍርካን በማስተሳሰር ለምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2020 አቋርጦት የነበረውን ከአዲስ አበባ ወደ ሞንሮቪያ የቀጥታ በረራ በዛሬው ዕለት ዳግም ጀምሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት አየር መንገዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።
ወደ ሞንሮቪያ ዳግም በረራ መጀመሩ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ባንግላዲሽ ዳካና ፖርት ሱዳን አዳዲስ መዳረሻ መፍጠሩ የአየር መንገዱን ሚና የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን በአየር ትራንስፖርት ለማስተሳሰር እየሰራ ሲሆን ላይቤሪያ በአፍሪካ ካሉ ሀገራት 41ኛ በከተማ ደረጃ ደግሞ ሞንሮቪያ 63ኛ መዳረሻ ሆነዋል ብለዋል።
ይህም የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የሰዎች እንቅስቃሴን በማሳለጥ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ የሀገራትን ትብብርና ተጠቃሚነት በማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወ ይገኛል ነው ያሉት።
ወደ ሞንሮቪያ በሳምንት ሶስት ጊዜ የሚያደርገው ቀጥታ በረራ እንግልትን እንደሚያስቀር ዋና ስራ አስፈጻሚው አመላክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በተመሳሳይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የመንግስታት፣ የባህል፣ የህዝብ ለህዝብና የምጣኔ ሃብት ትስስርን የበለጠ እንደሚያጠናክር ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካውያን በሚሰጠው የመንገደኞች እንዲሁም የጭነት አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የላይቤሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲርሊፍ ታይለር በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ላይቤሪያ በረራ መጀመሩ ሀገሪቱን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ያገናኛታል ብለዋል።
አየር መንገዱ በአህጉሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አድንቀው፥ በላይቤሪያና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝም ገልጸዋል።