የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤር ባስ A350-1000 አውሮፕላንን ተረከበ

You are currently viewing የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤር ባስ A350-1000 አውሮፕላንን ተረከበ

AMN – ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን በፈረንሳይ ቱሉዝ በተካሄደ ስነስርዓት ከኤርባስ ኩባንያ ተረክቧል።

በርክክብ ስነስርዐቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የኤርባስ ኩባንያ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተረከበው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገባም ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ሪፎርም ላይ መሆኗን አንስተዋል።

በአፍሪካ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀዋል።

አየር መንገዱ ከኤር ባስ ኩባንያ የተረከበውና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350-1000 አውሮፕላንም ለአየር መንገዱ ቀጣይ እድገት ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የኤ350-1000 አውሮፕላን ወደ ገበያው መግባት አየር መንገዱ የተያያዘውን ፈጣን እድገት በላቀ ደረጃ ለማሳለጥ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስገባት ፈር-ቀዳጅ መሆኑን በማንሳት፤ ኤ350-1000 አውሮፕላንም በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቅ ስኬት መሆኑን አክለዋል።

የኤር ባስ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ውተር ቫን ዌርሰች በበኩላቸው፤ ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350-1000 አውሮፕላን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2035 ስኬት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል ።

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመስራት ትልቅ ፍላጎት አለው ብለዋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሣይ ቱሉስ ተነስቶ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review