የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቻይናውያን ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻዎች ናቸው- ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር)

AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቻይናውያን ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ዋነኛ መዳረሻዎች መሆናቸውን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኃላፊው ይህንን የገለጹት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ጋር የቻናውያን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና እንዲጨምር ለማድረግ አዲስ አበባ በሚገኘው የቻይና ኢምባሲ በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡

በዉይይቱ ከኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር በተጨማሪ የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክን የማስፋፊያ ግንባታ ለማስጀመር ከኤምባሲው ጋር በትብብር በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ፡፡

የአዳማ ሁናን ፕሮጀክት የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ሲሆን አሁን ላይ ለግንባታው የሚያስፈልገው 125 ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የሁለቱን ሀገራት የኢንቨስትመንት ግንኙነት አወድሰዉ ሁለቱ ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረገድ አሁን ላይ የደረሱበት ሁኔታዎች የማይለወጥ ወዳጅነት ለዚህ ጥልቀት ማሳያ ነዉ ያሉ ሲሆን፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ማፅናት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና የቻይናውያን ባለሀብቶች ተሳትፎ በአብነት የሚነሳ መሆኑን የጠቆሙት ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) መንግስት የዉጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በተለይም በዉጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ያደረገው ማሻሻያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቻይናውያን ባለሀብቶችም ይህንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ፓርኮቹ ወዋለ ነዋያቸውን ስራ ላይ እዲያውሉም ኤምባሲው ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን መጠቆማቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ ከኤምባሲው ጋር በኢንቨስትመንት ፤ በሰዉ ሀይል ልማት እና በልምድ ልውውጥ ያሉትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል፡፡

ይህም በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ዉስጥ ለሚሰሩ የቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ይበልጡን ያግዛል ብለዋል፡፡

ቻይናውያን ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮች ውስጥ መዋለ ነዋያቸውን ስራ ላይ ለማዋል ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ቁጥር አንድ መሆኑን አንስተው ይህም የሀገራቱን ዘላቂ ወዳጅነት ይበልጡን አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን አማካሪው አውስተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review