የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበት 55ኛ ዓመት ተከበረ

You are currently viewing የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበት 55ኛ ዓመት ተከበረ

AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበት 55ኛ ዓመት በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት ተከብሯል።

ዕለቱ “55 ዓመታት ጠንካራ አጋርነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረ ሲሆን፣ በቻይና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ኢትዮጵያ እና ቻይና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በጋራ መተማመን፣ በመከባበር እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር ተፈራ የአዲስ አበባ -ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት እና የተለያዩ የሀይል ማመንጫ ጅምር ፕሮጀክቶችን በማውሳት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል።

የሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ቼን ሺያኦዶንግ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው የቻይና አጋሮች አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ትብብራቸውም ወደ በማንኛውም ሁኔታ የማይለወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት ማደጉን አመላክተዋል።

አያይዘውም ቻይና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች ዘላቂነት ያለው ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ኢምባሲ በተካሄደው በዚህ ዝግጅት የሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ የቢዝነስ ሃላፊዎች፣ የሚዲያ መሪዎች፣ የዳያስፖራ አባላት እና ተማሪዎች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review