የኢትዮጵያ እና ኩባን ጠንካራ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ መስከረም 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም በኩባ ሀቫና ተካሄዷል።
በጉባኤው ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ተሳትፏል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ እና ከሌሎች የአገሪቷ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ የአገራቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ከጃማይካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሚና ጆንሰን ስሚዝ፣ ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀነራል ኢንገር አንደርሰን ጋር ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ ትብብር ከመደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በደምና በመስዋዕትነት ጭምር ልዩ ታሪካዊ ግንኙነት ያለው መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
በትምህርት ዘርፍና ሌሎችም መስኮች ጠንካራ ትብብር ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውም ጥልቅ ቁርኝት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ ጋር በተደረገው ውይይትም የሁለቱን አገራት የቆየ ጠንካራ ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በሚኒስትሮች ደረጃ የምክክር መድረክ ለማካሄድ መስማማታቸውንም ነው የገለጹት።
የኩባ ፕሬዝዳንት በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ የስራ ጉብኝት እንዲደረግ ግብዣ ማቅረባቸውንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኩባ በተለያዩ መስኮች ይበልጥ በመተባበር የመስራትና የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላቸውን ትብብር ለማጎልበትም መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልምዷን ማካፈሏን ገልጸዋል።
የጂኦ ፖለቲካ አሰላለፎችን በመቋቋምና አብሮ በማደግ አገራት ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ከማድረግ አኳያ ወቅታዊነቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ በጉባኤው በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ስኬታማ ስራ ማከናወኗን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1975 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr
Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9
Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8
Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ