AMN- መስከረም 27/2017 ዓ.ም
አቶ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ የተመራውን የሩሲያ ፌዴሬሽን የልዑካን ቡድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
አቶ አገኘሁ ተሻገር ሁለቱ ሀገራት የረጅም ዘመን የታሪክና የባህል ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውና ይህ ስምምነት ፈጥኖ ወደተግባር እንዲገባ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው ምክር ቤቱ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አያያዝ ዙሪያ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚፈልግ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሩሲያን ድጋፍ እንደማይለያት የጠቀሱት አቶ አገኘሁ በብሪክስ አባል ሀገራት የሚወሱ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ተግታ እንደምትሰራ አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ ምኞት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የሩሲያው ሴናተር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ለሀገራቸው ሩሲያ ጠንካራ ወዳጅ ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ሀገራቸው በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህል ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመው የሩሲያን ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ መክፈት እንደምትፈልጉና ሩሲያ የብሪክስ አባል ሀገራት ሰብሳቢ በመሆኗ አባላቱ በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና የጽ/ቤቱ የማኔጅመንት ቡድን መገኘታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡