የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አስተማማኝ የገበያ ስርዓትን ከመፍጠር ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡-የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች

You are currently viewing የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አስተማማኝ የገበያ ስርዓትን ከመፍጠር ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡-የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች

AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አስተማማኝ የገበያ ስርዓትን ከመፍጠር ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በቅርቡ ተግባራዊ ከሆነው ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተገናኘ የፀደቀውና ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ አግኝቶ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አስተማማኝ የገበያ ስርዓትን ከመፍጠር ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችገበያ አማካሪ አቶ ሀብታሙ እሸቱ እንዳሉት ለዚህ ስራ ውጤታማነትና ማንኛውን ዜጋ ተጠቃሚ በመሆን እንዲሳተፍ ለማስቻል የግንዛቤ ስራው በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የግሉን ዘርፍ ለማበረታታትና አቅማቸው እንዲጎለብት በማድረግ ከፍ ሲልም ለአገር ኢኮኖሚ አስዋጽኦ ማበርከትን ዓላማን አድርጎ የተነሳ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ገበያው በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 አንቀጽ 31 መሰረት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የተቋቋመ ሲሆን ትኩረቱን የግሉ ዘርፍ ላይ ያድርግ እንጂ መንግስትና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተሳታፊ ለሚሆኑ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የስርዓቱ መነሻ በሃገር አቀፍ ደረጃ የካፒታል ገበያ መመስረት እንደሆነ ያነሱት አማካሪው የመገበያያ ስፍራው ደግሞ የሰነደ መዋእለ ነዋዮች ገበያ እንሚባል ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያ ስርዓት ገንዘብንና ኢንቨስተርን ወይም ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን የማገናኘት ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ሀብታሙ ይህም ከዚህ በፊት አስተማማኝ ያልነበረውንና በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ የተመሰረተውን ስርዓት በማስወገድ አስተማማኝ ገበያን የመመስረት ዓላማ ያደረገ ነውም ብለዋል፡፡

ዘላቂ የካፒታል ገበያን ለመፍጠር የሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ መመቻቸቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሞገስ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ለገበያው ስኬታማነት በአገር አቀፍ ደረጃ ምቹ ሁኔታዎች መኖር እንዳለባቸውም የኢኮኖሚ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

በሂደቱ ሁሉም አካላት በተለይም ማንኛውም ዜጋ ተጠቃሚ እንዲሆንና እንዲሳተፍ ለማስቻል የግንዛቤ ስራው በትኩረት መሰራት አለበት የሚሉት ዶክተር ሞገስ በዚህም መተማመን መፍጠር ቀዳሚው ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ከግለሰቦችና በዘርፉ ተሳትፎ ከሚያደርጉ አካላት ባለፈ በሃገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ግልጽ መረጃ ከማግኘት ጀምሮ ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠር እስከማደረግ ድረስ ሃገራዊ ጠቀሜታ እዳለውም አንስተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review