የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የትውልዱን መጪ ዘመን መሰረት ያደረገ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የትውልዱን መጪ ዘመን መሰረት ያደረገ ነው

AMN – መጋቢት 20/2017

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የትውልዱን መጪ ዘመን መሰረት ያደረገ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህር በርን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በባህር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ የማይል ይፋዊ አቋም እንዳላት አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ያንን የሚሸከም አማራጭ ወደብ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር በር አስፈላጊነትን በሚመለከት ወጣቶቹ እንደገለጹት፤አገሪቷ ካላት የህዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ ጥያቄው ወቅታዊና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ወጣት አብዱላዚዝ ሙዲን የባህር በር ማግኘት እንደ አገር ያለውን የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግሯል፡፡

ወጣት ኪሩቤል ለማ በበኩሉ፤ የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንደሚያስገኝ በመጥቀስ በተለይም የነገ አገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ ይሆናል ብሏል፡፡

የባህር በር ማግኘት እንደ ኢትዮጵያ ላለች ግዙፍ ሀገር አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ያለው ወጣት አብዲ ሁሴን፤ የተሻለች ሀገርና የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለሌላ ልማት ለማዋል ያግዛል ብሏል፡፡

ወጣት ጃንቦ ሁሴን በበኩሉ፤ ለሀገሪቷ ቀጣይ የዕድገት ጉዞና የወጪ ንግድ መሳለጥ የባህር በር አስፈላጊነት አጠያያቂ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡

የትውልዱን መጪው ዘመን ብሩህ ለማድረግ የባህር በር አስፈላጊነት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄው የወጣቱ የዘወትር ጥያቄ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ መጥቀሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review