AMN- ህዳር 12/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ “ለላቀ የፖሊስ አቅም ያደገ የጤና ተቋም ዋስትና ነው” በሚል መሪ ቃል የ2016 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ማጠቃለያ የምስጋና እና የዕዉቅና መርሃ- ግብር አካሄዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በመርሃ ግብሩ ላይ በሰጡት የሥራ መመሪያ ሆስፒታሉ በግዳጅ ላይ ጉዳት ከሚደርስባቸው የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም በክብር በጡረታ የተገለሉ እና ቤተሰቦቻቸው ጭምር የሚጠቀሙበት የጋራ ንብረታችን ስለሆነ ሆስፒታሉን ከነበረበት ችግር ውስጥ አውጥተን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርገናል።
ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚመለስ ነገር ስለሌለ የሆስፒታሉ አመራሮች መሪ ሆናችሁ የሆስፒታሉን ስታንዳርድ በማስጠበቅ ከዚህም በላይ አገልግሎቱን ከፍ በማድረግ ለውጡን ማስቀጠል አለባችሁ ሲሉ በአጽዕኖት ተናግረዋል።
አያይዘውም የጋራ ንብረታችን የሆነው ሆስፒታሉ በደንብ እንዲፀና ከምንም በላይ መጠበቅ አለበት ካሉ በኋላ የሆስፒታሉ አመራሮችና የህክምና ባለሙያዎች በግዳጅ ላይ ቆስለው የሚመጡትን አመራር እና አባላት ያለምንም መሰልቸትና ድካም 24 ሰዓት በሙያችሁ እያገለገላችሁ ስለምትገኙ ላቅ ያለ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
በሆስፒታሉ አገልግሎት የምትሰጡ ሐኪሞች እና በየደረጃው የተመደባችሁ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አገልግሎቱን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፤ ከሌብነት በፀዳ መልኩ በጥሩ ሥነ-ምግባር ሠራዊቱንና ቤተሰቦቹን በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የፖሊስ ሆስፒታሉ በየትኛውም ደረጃ በዶርሞችም ሆነ በቅጥር ግቢው ፅዳቱ ተጠብቆ ቆሻሻ የሚባይል ነገር የማይታይበት ቦታ እንዲሆን ሁሉም ተገልጋይና አገልጋይ ኃላፊነት ወስዶ መጠበቅ እንዳለበት አንስተው ይህንን የሚሸረሽር አመራርና ሠራተኛ በሆስፒታሉ ሊኖር እንደማይገባ ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ የጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዶ/ር አብረሃም ተፈራ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከሪፎርሙ በፊት ተቋሙን የማይመጥኑና ከሆስፒታሉ ባህሪ ጋር የማይሄዱ በአሮጌ ቆርቆሮ ቤቶች የታጨቀ የሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ሲስተም ከፍተኛ ችግር የነበረበት፣ ከደረጃ በታች የነበሩ የምግብ ማደራጃና ላውንደሪ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ችግር የነበረበት ሆስፒታል መሆኑን ገልፀዋል።
አያይዘውም የጤና አገልግሎት ዋና መምሪያው በጤና ሚኒስቴር መመዘኛ እና በሀገር አቀፍ የህክምና ጥራት መመዘኛ መስፈርቶች እጅግ የከፋ ደረጃ የተሰጠው እና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የነበሩበት እና የተሰጠውን ተልዕኮ በጥራት ለመፈፀም አዳጋች እንደነበረ አንስተው በ2016 በጀት ዓመት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብና ሌት ተቀን በተካሄደው የሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካኝነት ችግሮቹ ተቀርፈው ሆስፒታሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።