የኢትዮጵያ ፖሊስ በከፍተኛ ሁኔታ ወንጀልን መከላከል በሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል 116ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፖሊስ ቀንን በተመለከተ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበት 116ኛ ዓመት ላለፉት ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የምስረታ ቀኑን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሲምፖዚየም በነገው ዕለት እንደሚከፈትም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ታሪክ እና እየተገበረው ያለው የሪፎርም ስራን በተመለከተ ጽሁፍ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡
ከሲምፖዚየሙ ባለፈም የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ ቀን በደማቅ ሁኔታ በመስቀል አደባባይ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ባለፉት 7 ዓመታት ሪፎርም በማድረግ በኢትዮጵያ ፖሊስ ታሪክ ትልቅ የሚባል ለውጥ ማምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ህብረተሰቡ በቀጥታ ጥቆማ የሚሰጥበት የፌዴራል ፖሊስ መተግበርያ ጥቅም ላይ መዋሉን እና ይህም ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም የድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የወንጀል መከላከል ስራን የሚያግዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ሪፎርሙ የፌደራል ፖሊስ የሰው ኃይል ወቅቱ የሚጠብቀው የፖሊስ ቁመና ላይ እንዲደርስ እና በሎጂስቲክ አቅሙ ከፍ እንዲል ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡
የፖሊስ ስራ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ ማህበረሰቡም ወንጀልን በመከላከል በኩል እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡