የኢኮኖሚውን ሰንኮፍ የመንቀል ትልም

ከሰሞኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ አምባሳደርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ታዬ አጽቀሥላሴን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾማል። ፕሬዝዳንቱ በሁለቱ ምክር ቤቶች ፊት ባደረጉት ንግግር ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚው ጉዳይ ዋነኛው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንት ታዬ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ንግግር በ2017 በጀት አመት 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ በበጀት አመቱም የመንግስት ገቢን 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ማድረስ፣ ከሸቀጦች ወጪ ንግድ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ይሠራል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም ከኤክስፖርት ገቢ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እና በጥብቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ቁጥጥርና የገበያ ሰንሰለት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ የዋጋ ግሽበትን መከላከል ዋንኞቹ የኢኮኖሚው የትኩረት አቅጣጫዎች ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፣ በ2017 ዓ.ም ህገ ወጥ ንግድን መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡ ለመሆኑ ይህን ችግር መቅረፍ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው አንድምታ ምንድን ነው? እንደ ነዳጅ፣ ወርቅ፣ የቀንድ ከብት፣ ጫትን የመሳሰሉ ምርቶች ለህገ ወጥ ንግድ መጋለጣቸው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖስ ምን ይመስላል? ለችግሩ እልባት ለመስጠት ከማን ምን ይጠበቃል? የሚሉና መሰል ጉዳዮች ላይ የዝግጅት ክፍላችን የተለያዩ መረጃዎችን አካትቶ እንደዚሁም የዘርፉን ባለሙያ አነጋግሮ ተከታዩን ፅሑፍ አሰናድቷል፡፡

ኮንትሮባንድን መከላከል ከዓመቱ ወሳኝ ስራዎች መካከል አንዱ ነው

ለምጣኔ ሀብታዊና አገራዊ መረጋጋቱ እንቅፋቶች ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መሆናቸውን የመስኩ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያም  ለበርካታ ዓመታት ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በመሪዎች ደረጃ የሚመራ የተለያዩ አካላት የተካተቱበት ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ጭምር ብትሰራም አሁንም ድረስ ድርጊቱን መግታት አልቻለችም፡፡

የኢትዮጵያ ጉምሩክ አዋጅ የኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ የወጡ ህጎችንና መመሪያዎችን በመተላለፍ ዕቃዎችን ማስገባትን፣ በህጋዊ መንገድ የወጡትን በህገ ወጥ መንገድ መልሶ ማስገባትን፣ መያዝን፣ ማከማቸትን፣ ማዘዋወርን፣ ማስተላለፍን፣ እንዲገቡ ወይም እንዲወጡ ለማድረግ መሞከርን እንደዚሁም እነዚህን ዕቃዎችን መግዛትን፣ መሸጥንና ለዚህ ድርጊት ተባባሪ መሆንን ይከለክላል።

የወጭ ንግድ ስርዓቱን በመጋፋትም እንደ ቁም ከብት፣ የቅባት እህሎችና መሰል ምርቶችም ኮንትሮባንድ ድርጊት ሲጋለጡ መቆየታቸውን አዲስ ልሳን ጋዜጣ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሞያ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን ይናገራሉ።

ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ከተፈቀደ መጠንና ኮታ በላይ ምርትን ማዘዋወርና ማከማቸት፣ እጥረትን ለመፍጠር ምርት አከማችቶ መያዝ፣ ምርቶችን አላግባብ መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማዟዟር እንዲሁም የባንክ መላኪያ ፍቃድ ለሶስተኛ ወገን መሸጥ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማዳከም ለልማትና ለዕድገት የሚደረገውን ርብርብ እየተፈታተኑ የሚገኙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ስለመሆናቸውም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለማሳያ ያህልም የጉምሩክ ኮሚሽን በወርሃ ነሀሴ 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 244 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 43 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 287 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል የሚለውን ሪፖርት እዚህ ጋር መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫዎች፣ የግንባታ ግብዓቶች፣ ወርቅ፣ የምግብ ዘይት፣ የቁም እንስሳት፣ የጦር መሳሪያ እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የቅርብ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፣ ከውጭ የሚገባው ነዳጅ ሳይቀር ለሌብነትና ለኮንትሮባንድ ንግድ ብሎም ለብክነት ተጋልጠዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኪሩቤል ሰለሞን በተለይ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ግጅት ክፍል እንደገለፁት ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ የመንግስትን የበጀት መዳከም በከፍተኛ ሁኔታ ከማባባሱም ሌላ የመንግስት ባለስልጣናትን ለሙስና ያጋልጣል፡፡ በተለይ አሁን ከተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና አለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋማትን የመሳብ ጥረት አኳያ ህገ ወጥነቱ ተወዳዳሪነትን የሚያዳክም በመሆኑ ብርቱ ጥረት ያስፈልገዋል፡፡ መንግስት የጠሩ ህግጋትና ቁርጠኝነትን በመተግበር ህዝብ ያሳተፈ ርብርብ ማድረግ አለበት፡፡

ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የኑሮ ውድነትን በማባባስ ኢፍትሃዊነትን የሚያሰፍን ነው የሚሉት አቶ ኪሩቤል፣ የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ህጋዊውን የንግድና ኢንቨስትመንት ስርዓት እንዲሁም አንቀሳቃሹን የሚያውክ እንደመሆኑ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መታገል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም በገቢ ረገድ በህገ ወጥ መንገድ ወርቅና ሌሎች ምርቶች ወደ ውጭ የሚወጡ ከሆነ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የአገር ኢኮኖሚን ያዳክማል ብለው፣ መንግስት አገሪቱ የምታመነጨውን የኢኮኖሚ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ግብር መሰብሰብ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 

መንግስት ከቅርብ አመታት ወዲህ የታክስና ጉሙሩክ የአሠራር ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ መሻሻል ሲያመጣ ቢቆይም፣ አሁንም ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ የኢኮኖሚው ማነቆዎች ሆነው ቀጥለዋል። ከሰሞኑን የፓርላማ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዘደንት ታዬ፣ ህገ ወጥነትና ኮንትሮባንድን መከላከል ከዓመቱ ወሳኝ ስራዎች መካከል አንዱ ነው ማላታቸውም ለዚሁ ይመስላል፡፡

በአገሪቱ ፈተና ሆነው የቆዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ከ2016 በጀት አመት ጀምሮ ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ነው ያብራሩት፡፡

በያዝነው በጀት አመትም በዋናነት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢን ማሻሻል፣ የዘርፎች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የመንግስት የመፈፀም አቅምን ማጎልበት ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመት ህገ ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ከወዲሁ የተጀመሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን፣ በተለይም የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ፣ የምርቶች የጥራት ደረጃን መቆጣጠርና መሰል ስራዎች ስለመሰራታቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለማሳያ ያህል በሁሉም የአገሪቱ ማደያዎች የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ሲስተም የክፍያ አማራጮች ብቻ እንዲፈፀም ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡ የነዳጅ ሪፎርሙን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና ተደራሽነት አንፃር እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል፡፡

በሌላም በኩል በሀገር ውስጥ ተመርተውና ከውጪ ሀገር ተገዝተው በገበያ ላይ በሚገኙ እና የስጋት ደረጃቸው ከፍተኛ በሆኑ 48 የምርት አይነቶች እንዲሁም አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርት የወጣላቸውን ምርቶችን በሚያመርቱ 440 ፋብሪካዎች ላይ በ2017 በጀት አመት የጥራት ቁጥጥር ለማደረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

 “የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት አካል የሆነው በሀገር ውስጥ ንግድ ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የማክሮ ኢኮኖሚው ሪፎርም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ክልል በተሰሩ ስራዎች አላግባብ ዋጋ በጨመሩና ባከማቹ ከ70 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እርምጃ በመወሰዱ ገበያው ወደ ነበረበት መመለሱን አብራርተዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል መንግስት ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኪሩቤል ሰለሞን መክረዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review