አዲስ አበባ ያላትን አቅም ተጠቅማ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ጥረት እያደረገች ትገኛለች
ወጣት አቤሜሌክ ደጉ፤ ገና በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ሳለ የራሱን የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ሃሳብን ይዞ የተነሳ እና እሱንም ወደ ተግባር የለወጠ ብርቱ ወጣት ነው፡፡ “ጉራራ ቢዝነስ ግሩፕ” የሚባል ድርጅትን በመመስረት በሥራ አስኪያጅነት እየመራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ወደ ሥራ የገባው በ2010 ዓ.ም. ሲሆን፤ ፕላስቲክን መልሶ በመጠቀም እና የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ሥራ ላይ ተሠማርቷል፡፡
ስለድርጅቱ ሲያብራራ፤ እኛ ያቋቋምነው ድርጅት (ኢንተርፕራይዝ) ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ አንደኛው ጠቀሜታ ራሱን የቻለ ድርጅት ማቋቋም መቻሉ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ ሲሆን፤ የምርት ተደራሽነቱ እየሰፋ፣ ገቢው እያደገ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅሙ እየጎለበተ መሄድ መቻሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱ ለአካባቢ እና ተፈጥሮ ጥበቃ የራሱን ሚና መጫወት መቻሉ ነው፡፡ ድርጅቱ ለምርቱ የሚጠቀመው ግብዓት የወዳደቁ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶችን በመሆኑ፣ ለግብዓት ማሟያነት በሚሰበስበው ከፍተኛ መጠን ያለው የፕላስቲክ ተረፈ ምርት በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ብክለትና አደጋ ለመቀነስ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ ግልፅ ነው፡፡ በሦስተኛነት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ነው፡፡
በጉራራ ቢዝነስ ግሩፕ ተመርተው ለአገልግሎት እየበቁ ካሉት ምርቶች መካከል፡- ችግኞችን ለማፍላት የሚያስችለውን አፈር የሚሸከም (የሚያቅፍ) የፕላስቲክ ከረጢት፣ የኤሌክትሪክ ገመድ ማስተላለፊያ ፕላስቲክ ቱቦዎች (ኮንዲዩቶች)፣ የፍራፍሬ ማስቀመጫ የፕላስቲክ ሳጥኖች፣ የተፈጨ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከውጭ ሀገራት ይገቡ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ በራስ አቅም ወደመተካት ተሄዷል። ለዚህ ደግሞ ይህ ድርጅት የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልፆልናል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት የምታስገባቸውን የፕላስቲክ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶችን በብዛትና በዓይነት የመተካት ዓላማን ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፤ ከፕላስቲክ ተረፈ ምርት የግንባታ ግብዓትን የማምረት ውጥንም አለው፡፡

ድርጅቱ በቀን 24 ሠዓት በሳምንት ለስድስት ቀናት ይሠራል፡፡ በቀን 12፣ በማታው 12 በድምሩ ለ24 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡ በጊዜያዊነት ደግሞ 100 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ አማራጭ ሆኗል፡፡ በተለይ ችግኞችን ለማፍላት የሚያስችለውን አፈር የሚሸከም (የሚያቅፍ) የፕላስቲክ ከረጢት አምርቶ በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ላለው ገበያ ማቅረቡን የሚቀጥልበት ምቹ ሁኔታ እንዳለው ሥራ አስኪያጁ ይናገራል፡፡ ይህንንም ሲያብራራ፤ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ለድርጅቱ ምርት ዋነኛ የገበያ ዕድል ሆኖለታል፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እየተተከሉ በሚገኝባት ሀገር፤ ለችግኝ ማፍላት ውጤታማነት የሚያግዙ የፕላስቲክ ከረጢት ዓይነት ምርቶች ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ተግባሩ ወደ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የድርጅቱን ምርት ተደራሽነት እንዲሰፋ መልካም ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተስፋፋ የመጣውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ታሳቢ በማድረግ የድርጅቱን ምርት ተደራሽነት ወደ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን…) ለማስፋት ከወዲሁ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ሀገር በቀል የሆነውና በኢትዮጵያዊያን ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የተመሰረተው ሲምቦና አፍሪካ ሄልዝኬር (Simbona Africa Healthcare) ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን የሚያመርት ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ሀገራት ገበያ የሚቀርቡ የህክምና መሳሪያዎችን የመንደፍ እና የማምረትን ርዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል፡፡ የራስ አቅምንና ዕውቀትን በመጠቀም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ያሉ የጤና አጠባበቅ ተግዳሮትን ለመፍታት የሚያስችሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን በጥራትና በብዛት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው የሚደርስበትን አማራጭ በመፍጠር ሂደት ላይ ነው፡፡
ስለኩባንያው የምርት ሁኔታ ማብራሪያ የሠጠን የኩባንያው መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሃብታሙ አባፎጌ እንደሚያብራራው፤ ማዕከሉን በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ አራት በሚገኘው የኢንዱስትሪ ዞን ያደረገው ኩባንያው ከሚያመርታቸው ቁልፍ ምርቶች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ የመጀመሪያው የሕፃናት ማሞቂያ (Baby Warmer) ሲሆን፤ ይህ መሳሪያ ያለጊዜያቸው እና ዝቅተኛ ክብደት ባላቸው ጨቅላ ህጻናት ላይ ሃይፖሰርሚያን ለመከላከል የተሰራ ነው፡፡ ይህ መሳሪያ በውድ ዋጋ ከውጭ ከሚገቡ ሞዴሎች ጋር ተመጣጣኝ አማራጭ ይሰጣል። ሁለተኛው የአራስ የፎቶቴራፒ ክፍል (Neonatal Phototherapy Unit) ነው፡፡ ያለጊዜው ለተወለደ አራስ ሕጻን ሕክምና ተብሎ የተነደፈ፣ ይህ ክፍል ወጪ ቆጣቢ እና በአካባቢው የሚደገፍ ሆኖ ውጤታማ እንክብካቤን ይሰጣል። ሦስተኛው የአልትራቫዮሌት ማጽጃ ማሽን (Ultraviolet Disinfection Machine) ሲሆን፤ በሆስፒታል የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን ለመቀነስ የህክምና መሳሪያዎችን እና አከባቢዎችን በፀረ-ተህዋሲያን ለመበከል ተግባራዊ መፍትሄ ይሰጣል። የኦክስጅን ማጎሪያ (Oxygen Concentrator) ሌላኛው የሲንቦና አፍሪካ ኩባንያ ምርት የሆነው የሕክምና መሣሪያ ነው፡፡ መሣሪያው የኦክስጂን እጥረት ላለባቸው ታማሚዎች ተጨማሪ ኦክስጅንን የሚሰጥ ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሕክምና መሣሪያዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ሲሆን፤ ሲምቦና አፍሪካ ሄልዝኬር (Simbona Africa Healthcare) ምርቶቹን በሀገር ውስጥ የማምረት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የኩባንያው ምርቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም እንደ ቪልግሮ አፍሪካ (Villgro Africa) ካሉ ከሌሎች ሀገራዊና አሕጉራዊ ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል፡፡
ከውጭ የሚገባ ምርትን የመተካት ሀገራዊ እንቅስቃሴ
ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርትን ከውጭ ታስገባለች፡፡ ከምታስገባቸው ምርቶች ደግሞ ቀላል የማባሉት በሀገር ውስጥ አቅም ሊመረቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ አለፍ ሲልም ለውጭ ገበያ እስከመቅረብ የሚደርስ አቅም አላቸው፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ሥራዎች እየተከወኑ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው መርሃ ግብር ይጠቀሳል፡፡
ከውጭ ሀገር የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን እና ወደ ውጭ እስከመላክ ለመድረስ የሚያግዙ መሠረታዊ ተግባራት በመንግስት በስፋት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ከኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው በ2017 በጀት ዓመት ይፋ የተደረገ መረጃ ያመላክታል፡፡ እንደመረጃው ከሆነ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ምርትን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ የፋይናንስ ዘዴዎችን አውጥቷል። የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ቁልፍ ዘርፎችን በመለየት ቅድሚያ ሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል ግብርና (በተለይ የተመረቱ ምግቦችን፣ ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ምርቶችን በማምረት)፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ ፋርማሲዩቲካል እና የግንባታ እቃዎች ይገኙበታል። የሀገር ውስጥ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ለምሳሌ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩትን የምግብ ዘይት፣ የተቀነባበሩ ምግቦች እና ማዳበሪያዎች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ ይገኛል።

ከሠው ኃብት ልማት ጋር በተያያዘም፤ ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በተዘጋጁ የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አፍስሳለች። የኢትዮጵያ የማስመጣት ጥረቶች የሀገር ውስጥ ፍላጎቶችን በመተካት ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ገበያዎች እንድትገባ ለመርዳት የተነደፉ ናቸው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ ገበያ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ መንግስት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርጓል። እንደ ቡና ባሉ ውስን ምርቶች ላይ ጥገኛነቷን በመቀነስ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውንና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የምርት ዓይነቶችን በማብዛት የወጭ ንግዷን ለማስፋፋት ጥረት አድርጋለች።
የተገኙ ውጤቶች
የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለችው ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች በተለይም እንደ ምግብ፣ የግንባታ እና የፍጆታ እቃዎች የመሳሰሉት በመጠናቸው ቀስ በቀስ እየቀነሱ መጥተዋል። እንደ ሲሚንቶ ያሉ ወሳኝ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በማደግ ላይ ናቸው። የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች አብዛኛውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት የማሟላት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ሂደት ከሚያስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ለዜጎች የሥራ ዕድል በብዛት መፍጠር መቻሉ እንደሆነ የሚናገሩት ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሃሳባቸውን ያጋሩት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ወረታው በዛብህ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ሃብት ያላት ሀገር ነች፡፡ ይህንን ሃብት በማልማት ከራሷ አልፎ ለውጭ ሀገር ገበያ ማቅረብ ትችላለች፡፡ ይሁን እንጂ ከግብርና ውጤቶች ጀምሮ በርካታ ምርቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላር በማውጣት ገዝታ ትጠቀማለች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደመንግስት የተያዘው አቅጣጫ እና እሱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
መንግስት ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል፡- ማምረቻ (ማኑፋክቸሪንግ) እና ግብርናው ተጠቃሽ መሆናቸውን ያነሱት ወረታው በዛብህ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ዘርፎች ለሀገር ወሳኝ የሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ አጋዥ ከመሆናቸው በላይ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዜጎች አዳዲስ ሥራዎች የሚፈጥሩና የፈጠሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች እያደጉ በሄዱ ቁጥር የምርት ፍላጎትን ለማሟላት የሚያስፈልገው የሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ ስለሚመጣ፤ በወጣቱ ላይ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና የማምረቻ (የማኑፋክቸሪንግ) መስፋፋት በቀጥታ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባለፈ፤ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ ሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት ያሉ ረዳት አገልግሎቶችን እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚሠራውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሳልፎ መተግበር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳ፣ ኬሚካል፣ የግንባታ እቃዎች፣ የማምረቻ ቴክኖሎጂ እና ከውጭ የሚገቡ የምግብ እና መጠጦችን ጨምሮ ቁጥራቸው 96 የሚደርሱ የምርት ዓይነቶችን ለይቷል። የስትራቴጂክ እቅዱ ሦስት ዓመታት ውስጥ (ከ2016 እስከ 2019 ዓ.ም) ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን የምግብ እና መጠጥ ምርቶች እንዲሁም የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ሙሉ በሙሉ ለመተካት አልሟል፡፡
አዲስ አበባስ ምን ትመስላለች?
የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባም ያላትን አቅም ተጠቅማ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ በጥረቷም አበረታች ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ነች፡፡ “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ- አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ባሳተፈ መልኩ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል። አውደ ርዕዩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ ነው። ከተማዋን “የኢንዱስትሪ ማዕከል እናደርጋለን” ስንል ፈጠራን በማበረታታት እና አምራቾችን በመደገፍ ጭምር ነው። ፋይናንስ በማቅረብ፣ የመስሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ መሠረተ ልማትን በማሟላት እና አስፈላጊ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት ለአምራቾች ድጋፍ እየተደረገ ነው። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርታማነት እንዲመለሱ አድርጎል። በመጪዎቹ ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪው የበለጠ እንዲያድግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንኑ ሀሳብ የሚያጠናክር ማብራሪያ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርትን ለከተማዋ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት አቅርበዋል፡፡ በገለጻቸውም፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ቁጥራቸው 1 ሺህ 671 የሚሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርበዋል፡፡ ጥቅል የምርት መጠኑ ከ725 ሚሊዮን 480 ሺህ ቶን በላይ ሲሆን፤ በዚህም ከ490 ሚሊዮን 630 ሺህ ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቁጥራቸው 184 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደውጪ ልከዋል፡፡
ለዚህ ውጤታማነት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በመገንባት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም ያሉባቸውን ችግሮች መፍታት ላይ መንግስት ትኩረት መስጠቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት ከሆነ፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጨመር ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማጎልበት እና የሚያነሷቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን መፍትሄ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ በዚህም የመብራት፣ የውሃ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች ለነበሩባቸው 231 ኢንዱስትሪዎች መፍትሄ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለ276 ኢንዱስትሪዎች የካፒታል ሊዝ ቀርቦላቸዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሰው አውደ ርዕይ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ገቢ ምርትን በመተካት፣ ኤክስፖርትን በማሳደግ፣ የስራ ዕድልን በመፍጠርና ተወዳዳሪ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው። የኢንዱስትሪ ዘርፉን በመደገፍ እና በሁለንተናዊ ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ተግባር አከናውኗል።
እንደከተማ ብሎም እንደሀገር ተኪ ምርቶችን በማምረት ሂደት ውስጥ እየታየ ያለውን ውጤታማነት ለማስቀጠል መሠራት ስለሚገባቸው ተግባራት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ወረታው በዛብህ (ዶ/ር) ምክረ ሃሳቦችን ሰጥተዋል፡፡ በተኪ ምርት ማምረት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን አቅም ማጎልበት፤ ያለባቸውን የፋይናንስ፣ የመሥሪያ ቦታ እና መሰል ችግሮች መፍታት፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብ እና ማሳደግ፤ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የሀገር ውስጥ ገበያን እንደሁነኛ አማራጭ መጠቀም ወይም ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርት እንዲኮራና እንዲጠቀም ማስቻል ይገባዋል፡፡ በሀገር ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ የሠላም መደፍረስ እና የፀጥታ ችግሮች መፍትሄ መስጠትም የመንግስት ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት። ይህ እንዲሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ