የእሁድ ገበያዎች አገር አቀፍ የደረጃ መስፈርት ወጣላቸው

You are currently viewing የእሁድ ገበያዎች አገር አቀፍ የደረጃ መስፈርት ወጣላቸው

AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም

የእሁድ ገበያዎች አገር አቀፍ የደረጃ መስፈርት የወጣላቸው መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የእሁድ ገበያ አምራቾችን፣ አቅራቢዎችንና ሸማቾችን ያለደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ በማገናኘት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ አማራጭ ገበያ ሆነው እንዲያገለግሉ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መስከረም ባህሩ እንደገለጹት፣ የእሁድ ገበያዎቹ ተቀራራቢና ወጥነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ለሸማቹ ለማቅረብ እንዲቻል ለማድረግ የደረጃ መስፈርቱ ተዘጋጅቷል፡፡

መስፈርቱ በዋናነት ተግባራዊ የሚሆነው በእሁድ ገበያዎቹ የሚቀርቡ በ6 የምርት አይነቶች ላይ ሲሆን እነሱም አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ አገዳና የሰብል ምርቶች፣ የእንስሳት ተዋፅኦ እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ለእሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ የምርት አይነቶች በአራት ምድብ ተከፍለው ሳይቀላቀሉ ንፅህናቸውን በጠበቀ መልኩ ለሽያጭ እንዲቀርቡ የሚያደርግና ስለአቅራቢዎች፣ መሸጫ ቦታዎችና ሼዶች የመሸጫ ዋጋ ሁኔታን በተመለከተ በደረጃ መስፈርቱ የተካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የደረጃ መስፈርቱ በብሄራዊ የደረጃዎች ካውንስል የፀደቀ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review