የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ

You are currently viewing የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ

AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂን ሊኩ ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂን ሊኩን ጋር በኢትዮጵያ መንግስትና በባንኩ መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክና በገንዘብ ሚኒስቴር መካከል ስለሚኖረው ትብብር ከባንኩ ፕሬዚዳንት ጋር በስፋት መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷን ለማፋጠን በተለይ አንደ ሀገር እየተሰራ ባለው የረጅም ጊዜ የእድገት ፕሮግራም፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ስላለው ሚና፣ ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለመፍጠር ስለሚደረገው ጥረት መመካከራቸውን አስረድተዋል፡፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ፋይናንስ የሚያደርግ ግዙፍ ተቋም በመሆኑ አዲሱን የኢትዮጵያ ኤርፖርት ግንባታና የታዳሽ ሀይል ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንና በነዚህ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂን ሊኩን በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘታቸውና ከገንዘብ ሚኒስትሩ ጋር ፍሪያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ማስረዳታቸውንም ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ባንኩ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ከአለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በአጋርነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የወደፊት ብሩህ ተስፋ እምነት እንዳላቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መልካሙን ሁሉ እንደሚመኙ መግለጻቸውም ተጠቁሟል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review