AMN- ጥር 1/2017 ዓ.ም
የጤናማ እናትነት ወር በሀገራችን ለ19ኛ ጊዜ በተያዘው ጥር ወር እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በጥር ወር በሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ህመምና ሞትን ለማስቀረት የቅድመ ወሊድና ድህረወሊድ ክትትልና ህክምና አገልግሎትን ጨምሮ እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲወልዱ እንዲሁም የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የእናቶች እና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች ትልቅ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ያስታወሱት ዶ/ር መቅደስ፤ አሁንም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው የጤና ጉዳዮች ቀዳሚው እንደሆነ አስረድተዋል።
በተለይም የመጀመሪያ ደረጀ የጤና ክብካቤ እና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማጠናከር የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከእርግዝና በፊት የሚሰጥ የጤና እንክብካቤ አገልግሎትን በማሳደግ፤ የጤና ባለሙያዎች በቤተሰብ ደረጃ ትምህርት እና የቅድመ እርግዝና ጤና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉም ተብሏል።
በወሊድ እና በምጥ ወቅት የእናቶች ሞት እንዳይከሰት የደም አቅርቦትን እንዲሁም የአምቡላንስ አገልግሎትን ለማሳደግ በቅርብ ግዜ የ370 አምቡላንሶች ድጋፍ ለክልሎች መደረጉን አስታውሰዋል።
የመድሃኒት አገልግሎት እንዳይቋረጥ ለማድረግ የሃገር ወስጥ የመድሃኒት ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸዉ ሁሉ ልማዳዊ አሰራሮችን በማስቀረት ለእናቶች እና ህጻናት ጤና ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሚዲያ ባለሙያዎች በጥር ወር የሚከበረውንና ጤናማ እናትነትን ሁል ግዜ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሯ መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።