አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2015 በተፈጥሮ ታይሮይድ የተባለ የፊተኛው አንገታችን አካባቢ ያለ የሰውነት ክፍል ሲያብጥ ወይም ሲተልቅ እንቅርት ይባላል፡፡
ነገር ግን አንገት ላይ ያለን እባጭ ሁሉ እንቅርት ነው ማለት ስለማይቻል ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መለየት እንደሚያስፈልግ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሸምሴ ሸውሞሎ ተናግረዋል፡፡
የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ እንቅርት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚፈጠር ይናገራሉ፡፡
እነሱም በአብዛኛው ጊዜ የአዮዲን እጥረት፣”ግሬቭስ ዲዚዝ”፣ኢንፌክሽን (ታይሮይድ በኢንፌክሽን ሲጎዳ)፣ለአዕምሮ ጤና የሚታዘዙ መድሃኒቶች፣ ብግነት እና ካንሰር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የእንቅርት ምልክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ቢለያዩም÷በአጠቃላይ ግን የአንገት ላይ እባጭ፣ የረጅም ጊዜ ሳል ፣ መዋጥ መቸገር፣የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ሲርሲር የሚል ድምጽ ያለው ሳል እና ትንታ ጥቂቶቹ መሆናቸውን ዶክተር ሸምሴ ተናግረዋል፡፡
በአዮዲን ዕጥረት የሚመጣውን እንቅርት በአዮዲን የበለፀገ ጨው በመመገብ እንዲሁም አዮዲን ያላቸውን ምግቦችን በመመገብ መከላከል እንደሚቻል የሚናገሩት የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ ከዚህ ምክንያት ውጭ የሚመጡት ግን ከታካሚው ቁጥጥር ውጭ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ህክምናውም እንደ መንስዔው የሚለያይ ሲሆን÷ ቀላል እንቅርት ወይም መጠኑ ትንሽ፣ ካንሰር ያልሆነ ፣ ከመደበኛ በላይም ሆነ በታች የታይሮይድ ሆርሞን የማያመነጭ ከሆነ ሕክምና ሳያስፈልገው ክትትል ብቻ በቂ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ምንም የታይሮይድ ሆርሞን የማያመነጭ፣ በጣም አነስተኛ የሚያመነጭ እንዲሁም ብዙ የሚያመነጭ ከሆነ እንደ አይነቱ የፓቶሎጂ፣ የደም፣ የአንገት አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን፣ኤም አር አይ ምርመራዎች እንደሚሰጡም ነው የሚናገሩት።
በዚህም በህክምና ባለሙያ ታይተው የተለያዩ የታይሮይድ ሆርሞን ለማስተካከል ከሚወሰዱ መድሃኒቶች ጀምሮ እስከ ቀዶ ህክምና በየደረጃው ህክምናዎች ይሰጣሉም ነው ያሉት የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ፡፡
እንቅርት በጊዜው ካልታከመ ካንሰር ከሆነ ወደ አየር ቧንቧ በመዛመት ለማስወጣት አስቸጋሪ ይሆንና እስከ ህልፈት ሊያደርስ እንደሚችልም ይገልጻሉ።
ልብ ድካም እና አንዳንድ ጊዜም በሴቶች ላይ የወር አበባ መዛባት እና መሃንነት ሊያመጣ እንደሚችልም ይጠቅሳሉ።