የእውቀት ደጅ እንቅፋቶች

You are currently viewing የእውቀት ደጅ እንቅፋቶች

• አሁንም በከተማዋ በ53 ትምህርት ቤቶች  ዙሪያ አዋኪ  ድርጊቶች ይገኛሉ

የትምህርት ጥራት የሁሉንም የጋራ ጥረት ይሻል፤ መንግስት የበኩሉን ሚና ለመወጣት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ ሲተገብር ይታያል፤ የትምህርት ጥራትን፣ ተደራሽነትና ተሳትፎን ለማሳደግ በተለይ የመምህራንን ሙያ በማጎልበት፣ ለመማር ማስተማሩ አጋዥ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ ስራዎችን  እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ሲተገበር በቆየው ‘ትምህርት ለትውልድ’ መርሃ ግብር የሚታዩ ለውጦች መምጣት ችለዋል፡፡

ነገር ግን አሁንም በከተማዋ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የመማር ማስተማር ስርዓቱን የሚያውኩ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡ ይህም በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡

ለእነዚህ አዋኪ ተግባራት ተጋላጭ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የሜይዴይ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 የሚገኘው የአዲስ አምባ ቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባሉ የመማር ማስተማር ሂደት እንቅፋቶች ዙሪያ ቅኝት አድርጓል፤ የየትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ አነጋግሮም ተከታዩን ፅሑፍ አዘጋጅቷል፡፡

ዙሪያውን በተለያዩ አዋኪ ድርጊቶች የተከበበው የሜይዴይ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

የአዲስ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እሱባለው ለገሰ፣ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉ በመሆኑ የተለያዩ ድምፆች ክፍል ውስጥ ድረስ ስለሚሰማ እንደሚረበሽ ተናግሯል፡፡ ተማሪው በማብራሪያው፣ “ትምህርት ቤቱ መንገድ ዳር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመንገዱ ላይ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች በቀጥታ ያውኩኛል፡፡ በተለምዶ ጀብሎ የሚባሉ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች፣ የታክሲ ረዳቶች፣ የተሽከርካሪዎች ድምፅና ጥሩንባ የመሳሰሉ ድምፆች ክፍል ድረስ ስለሚሰሙ የመምህራንን ድምፅ ለመስማት እስኪያዳክተኝ ይደርሳል” ብሏል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 የሚገኘው የአዲስ አምባ ቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዮሐንስ ተስፋዬ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ የንግድ ቤቶችና ሌሎች አዋኪ ድርጊቶች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ በዚህ ሳቢያም ከፍተኛ ድምጽ ስለሚፈጠር ትምህርቱን በአግባቡ እንዳይከታተል እንዳደረገው ይገልጻል፡፡

በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ጫት ቤቶች፣ የተሽከርካሪዎች ጡሩምባ፣ የሙዚቃ ድምጽ፣ ምግብ ቤቶች፣ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ መኖሩን እና የተለያዩ ግብይቶች እንደሚከናወኑም በመናገር፣ እነዚህ አዋኪ ድርጊቶች በትምህርት ሂደቱ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ በመሆናቸው እንዲቀረፉ ጠይቋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የሜይዴይ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡ መሃል  ከተማ መርካቶ በሚገኘው በዚህ ትምህርት ቤት በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ከ500 የሚበልጡ ተማሪዎች ቢኖሩም በዙሪያው ባሉ የጫትና ሺሻ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ መጠጥና ንግድ ቤቶች ሳቢያ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት አለመኖሩን ነው ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አጠቃላይ ማህበረሰብ ዘንድ ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

በትምህርት ቤቱ የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው መቅደስ ሃይሉ፣ በትምህርት ቤታቸው አካባቢ የመማር ማስተማሩን ተግባር የሚያውኩ መጠጥ ቤቶችና ጫት መሸጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ ጠቁማ፣ ከንግድ ቤቶቹ የሚወጣው ከፍተኛ ድምፅ በመማር ላይ እያሉ እንደሚረብሻቸው ተናግራለች፡፡

በትምህርት ቤት አካባቢ የሚከፈቱ የመጠጥ መሸጫዎችና ሌሎች አዋኪ ተግባራት ተማሪዎችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመሯቸው ይችላሉ የምትለው ተማሪዋ፣ እንደዚህ አይነት አጓጉል ተግባራትን ላለማከናወን ቀዳሚው የራስና የቤተሰብ ጥረት ቢሆንም በተለይ ተማሪዎች ጓደኛ መምረጥ ወጣ ያለ ባህሪ ከሚያሳዩ ልጆች መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ሌሎች ያነጋገርናቸው ተማሪዎችም በትምህርት ቤቱ ዙሪያ የሚከናወኑ በርካታ እንቅስቃሴዎችና አዋኪ ድርጊቶች ሳቢያ በትምህርት አቀባበላቸው ላይ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የ8ኛ ክፍል ተማሪው ሙሉቀን ተሾመም በአቅራቢያው ከፍተኛ ድምፅ በማውጣት የትምህርት ሂደቱን የሚያውኩ መጠጥ ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ተቋማት ከመኖራቸውም ሌላ በተለይ የትምህርት ቤታቸው አጥርን ተደግፈው ከተሰሩ መኝታ ቤቶች የሚመጣ የሲጋራ ሽታ እንደሚረብሸውና ይህ ችግርም እንዲቃለልለት ጠይቋል፡፡

ትምህርት ቤቱ መርካቶ መሃል የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ንግድም ሆነ በመንገዱ ላይ የሚከናወኑ የተሽከርካሪና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች በቀጥታ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያውኩ ናቸው የሚለው ተማሪው፣ በተለይ ወደ ትምህርት ቤቱ የመግቢያ በር አካባቢ ያለው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መግቢያና መውጫ ሰዓት በእጅጉ እንደሚያስቸግር ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይም በዚያው ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ኢምራን ኑሩሁሴን በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ጫት ቤቶች፣ የተሽከርካሪዎች ጡሩምባ፣ የሙዚቃ ድምጽ፣ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ግብይቶች የሚከናወኑባቸው የንግድ ተቋማት መኖራቸው ትምህርቱን በአግባቡ ለመከታተል እንቅፋት መፍጠራቸው ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ያለእድሜአቸው በአጓጉል ሱሶች እንዲጠመዱ በር የሚከፍት በመሆኑ ከወዲሁ ችግሩን ለመከላከል መትጋት ይገባል ነው ያለው፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አብረሃም ጥላሁን በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ያሉ ዋንኛ አዋኪ የሚባሉ ድርጊቶች እለት ተእለት እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አለመምጣታቸውን ነው የሚያስረዱት። ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ግብይት በሚካሄድበት የመርካቶ ገበያ አቅራቢያ የሚገኝ አንደመሆኑ በዙሪያው በርካታ መኝታ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፣ ይህም ተማሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ላይ ችግር ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አልጋ የሚከራዩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ከመጠን በላይ አልኮል የወሰዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አጭሰው ወደትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ በሚጥሉት የሲጋራ ቁራጭ ሳቢያ በተደጋጋሚ እሳት ተነስቶ ቤተመፃፍቱን ጨምሮ ሌሎች ክፍሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ያነሱት ርዕሰ መምህሩ፣ ባለፈው አመት እና ዘንድሮም  የትምህርት ዘመን በዚህ መልኩ የእሳት አደጋ ማጋጠሙንና ማህበረሰቡ ተረባርቦ እንዳጠፋው ተናግረዋል፡፡

በዙሪያው ካሉ መኝታ ቤቶች በተጨማሪም ከንግድ ቤቶች የሚወጣው ከፍተኛ ድምፅ፣ ፑል ቤት፣ ጫት ቤቶችና ሌሎችም የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያደናቅፉ አዋኪ ድርጊቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ትምህርት ቤቱን ከአዋኪ ድርጊቶች በመከላከል ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመፍጠር ከወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ፖሊስ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ መንገድ ዳር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ተማሪዎች ላይ ጫና የሚያሳድሩ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ፣ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው የወረዳና የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች እና ለከተማዋ ትምህርት ቢሮም በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አለመገኘቱን ነው የነገሩን።

ይልቁንም በውስጥ አሰራር በግቢው ያሉ ተማሪዎችን ባህሪ ለማረቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት በተደረገው እንቅስቃሴ የተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያዎችን በመተግበርና በማሰልጠን ወጣ ያለ ባህሪ ያላቸው ተማሪዎች ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብሩክ ተክለማርያም በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤቶች ዙሪያና አካባቢ የሚፈፀሙ አዋኪ ተግባራት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ብሎም በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ እንቅፋት የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ክፍለ ከተማው ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት እንቅፋት የሚፈጥሩ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እነኝህ ችግሮች እልባት እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ብሩክ፣ በሜይዴይ ቅድመ አንድኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ከአዋኪ ድርጊቶች ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑንና ችግሩን ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ድርጊቶች ጋር ተያይዞ በቅድሚያ ከተሰሩ ስራዎች ዋንኛው አዋኪ ድርጊቶችን መለየት ሲሆን፣ በዚህም በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ጫት ቤቶች፣ ቁማር ማጫወቻ (ቤቲንግ) ቤቶች፣ ጠጅ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶችና መሰል የንግድ ተቋማት፣ የተሽከርካሪ መጠገኛ ጋራዦች፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ የድምፅ ብክለት ያላቸው የስራ መስኮች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡  በቅንጅት በተሰራው ስራም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም ከ2 ሺህ 500  የሚበልጡ አዋኪ ድርጊቶችን ከትምህርት ቤቶች አካባቢ ማስወገድ ተችሏል፡፡

ኃላፊው አክለውም፣ ክፍለ ከተማው ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደመሆኑ በበርካታ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈፀሙ ለመማር ማስተማሩ ሂደት አመቺ ካልሆኑ አዋኪ ተግባራት አብዛኛዎቹን የማፅዳት ስራ እየተሰራ ነው ብለው፣ የሜይዴይ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካካለኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ አንዳንዶቹ ካላቸው ነባራዊ ሁኔታ፣ ካሉበት አቀማመጥና የከተማ ማዕከል ላይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ችግሩን  ማስወገድ አለመቻሉን ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

በተለይ የገዘፈ ውጫዊ ችግር ያለበት የሜይዴይ ትምህርት ቤት ከአንድም ሁለት ጊዜ በዙሪያው አዋኪ ድርጊት በሚፈፀምባቸው ንግድ ቤቶች ሳቢያ የእሳት አደጋ እንደደረሰበት ጠቁመው፣ በዙሪያው ያለውን የገዘፈ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡ ሰፊ የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠርና አጠቃላይ እንደ አስተዳደርም አካባቢን ከመቀየር ጋር በተያያዘ በሚሰሩ ስራዎች ችግሩ ሙሉ በሙሉ ይስተካከላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ይመር በትምህርት ቤቶች ያሉ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል ከማህበረሰቡና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው በቅርቡ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ባደረገው ጥናት ወደ 53 በሚጠጉ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ መጥጥና መኝታ ቤቶች፣ ፑል፣ ቤቲንግ፣ ጆተኒና ከረንቡላ ማጫወቻ፣ ጫትና ሺሻ ቤቶች፣ የተሽከርካሪዎች ድምፅ፣ የጎዳና ላይ ንግድ እንዲሁም ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች፣ ወፍጮ ቤቶች መኖራቸው የተለየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለፈው አመት በትምህርት በቶች አቅራቢያ ያሉ የቤቲንግ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ መኝታና መሸታ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከ4 ሺህ 600 በላይ ተቋማት እንዲታሸጉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ሃላፊው አክለውም በያዝነው በጀት ዓመት ወደ 38 በሚጠጉ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም በተደራጀ አግባብ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮም አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቋል። የቢሮው ሀላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፤ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ የተገኙ 879 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመው፣ እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ 184 ጫት ቤቶች፣ 48 መጠጥ ቤቶች፣ 12 ፔንሲዮኖች፣ 112 ጠላና መሰል አልኮል የሚሸጥባቸው ግሮሰሪዎች፣ የድምፅ ብክለትን ያስከተሉ 122 እንድሁም 220 የቆሻሻ እና መሰል አዋኪ ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review