AMN-ታህሣሥ 26/2017 ዓ.ም
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ የተገነባውን ኩሪፍቱ ሪዞርትና የአፍሪካ መንደር መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
አቶ ሽመልስ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ በተለያየ ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት አውጥታ መጠቀም እንድትችል ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል።
የቱሪዝም ሴክተሩ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዉ መንግሥት በራሱና የግል ዘርፉን በማስተባበር በሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስፋፋት ጥረት አድርጓል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የኩሪፍቱ ሪዞርት ለሀገሪቱ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝምን ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ አቅም ያለቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤት አቶ ታድዮስ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ የቡራዩ ኩሪፍቱ ሪዞርት እና አፍሪካ መንደር የአፍሪካ አንድነትን፣ ብዝሃነትን እና ድንበር የለሽ አቅምን ያሳየ መዳረሻ ነው።
ሪዞርቱ በ163 ካሬሜትር ላይ ያረፉና ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት የሚወክሉ 54 የማረፊያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ፤ የማረፊያ ክፍሎቹ በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን ጥበብ፣ ባህል እና ወግ ለማንፀባረቅ በጥንቃቄ መሰራቱ ተመልክቷል ።
ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚያገለግሉና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ዘጠኝ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፤ 1ሺህ የሚጠጉ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችል ሁለገብ አዳራሽ፣ ባሮች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ ስፓ፣ ጂምናዚየም እንዳለው ተገልጿል ።
የኩሪፍቱ ሪዞርትና አፍሪካ መንደር የአዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነት በሚመጥን መልኩ በከፍተኛ ጥረት ተገንብቶ መጠናቀቁ ተነግሯል ።
ሪዞርቱ በቋሚነት ከ800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተገለፀ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሥራውን ሲጀምር የሥራ ዕድል የሚፈጥርላቸው ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ተነግሯል።
የሪዞርቱ ባለቤት አቶ ታድዮስ በግንባታው ሂደት ድጋፍ ላደረገላቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሰደር ምስጋኑ አርጋ፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሰደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሀላፊዎች መገኘታቸውን ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።