የከተማችን ሠላም ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆነው ህዝቡ የሠላም ባለቤት እንዲሆን በመሠራቱ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የከተማችን ሠላም ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆነው ህዝቡ የሠላም ባለቤት እንዲሆን በመሠራቱ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ሠላም ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆነው ህዝቡ የሠላም ባለቤት እንዲሆን በመሠራቱ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እያካሄደ ባለው የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ ተገኝተው ከአባላቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሠላም አስተማማኝ መሆን መንግስት ወንጀልን በመከላል ረገድ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመሥራቱ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በዚህም የደረቅ ወንጀል ከአምናው አንፃር በ33 በመቶ ቀንሷል ብለዋል፡፡

ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ወንጀለኞችን በመያዝ በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራ ወንጀል ለመከላከል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች፣ ቀደም ሲል በፒያሳ፣ 4 ኪሎ፣ ቀበና፣ ቦሌ እና ሲኤምሲ አካባቢ የነበሩ የንግድ ሱቆች በሁለት ብረት በር እና ሻተር ይዘጉ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ወርቅ ቤቶችን ጨምሮ በመስተዋት በር ነው የሚዘጉት ብለዋል፡፡

መንግስት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ትላልቅ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በደህንነተ ካሜራ ውስጥ እንዲሆኑ በማድረግ ለወንጀል መከላከል ተግባር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን አብራረተዋል፡፡

መንግስት ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችም በመኖሪያቸው ባስገጠሙት ካሜራ የወንጀል ድርጊት ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ትብብር እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በተለምዶ ሿሿ ተብሎ የሚጠራ የወንጀል አይነት፣ የቅሚያ፣ የተደራጀ ዘረፋ እና መሠል ወንጀሎች በመከታተል አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሚገኝ እና በቀጣይም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review