የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የከተማዋን የትራፊክ ቁጥጥር እና ፓርኪንግ አስተዳደር ሥርዓት በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲተገበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከማንዋል ወደ ዲጂታል የሚያሸጋግር ሶፍትዌር አበልፅጎ ለትግበራ ማብቃቱ የሚታወስ ሲሆን የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲመራ እና እንዲያስተዳድር በተሰጠው ሕጋዊ ኃላፊነት ኢንፍራቴክ ሶፍትዌር አበልፃጊ ከተባለ ተቋም ጋር በመሆን በከተማዋ ውስጥ የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያቸውን እንዲሁም የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያን ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከፍሉበት ሶፍትዌር በማበልፀግ የትራፊክ ቅጣትንና የፓርኪንግ ክፍያን የሚያዘምን አሠራር አስጀምሯል፡፡
የበለፀገው ሶፍትዌር አውቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም በመባል የሚገለፅ ሲሆን የሶፍትዌሩ መበልፀግና ወደ ትግበራ በይፋ መግባቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ እንዲሁም የአካል እና የሥነ-ልቦና ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች ለመታደግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በሲስተሙ እስካሁን ድረስ 600,000 ተሸከርካሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን የዲጂታል ማሻሻያው የትራፊክ ቁጥጥርን፣ የፓርኪንግ አገልግሎትንና አጠቃላይ የከተማዋን የትራፊክ ሥርዓት በማስተዳደር የትራንስፖርት ሥርዓቱን የሚያዘምን ነው፡፡

የማንዋል አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀረው ይህ ቴክኖሎጂ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕግ ሲጥሱም ሆነ ለሚያገኙት የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አስቀድሞ ስለ ተሽከርካሪዎች መረጃ ከአዲስ አበባ አሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን መዝግቦ በያዘው መረጃ መሠረት ምዝገባ ያካሂዳል፡፡
ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ የሆነው ሶፍትዌር ዘመናዊ የትራፊክ ሲስተምን ለኅብረተሰቡ የሚያስተዋውቅ እና የተሻሻለውን የመንገድ ትራንስፖርት መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 557/2016 ተግባራዊ በማድረግ የቁጥጥር ሥራን የሚያዘምን ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በፓድ ሲካሄድ የነበረውን የትራፊክ ቅጣት እና የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያን ወደ ዲጂታል በመቀየሩ የተገልጋይን እንግልት የሚያስቀር፤ በየዓመቱ ለፓድ ህትመት የሚወጣን ከ17 ሚሊየን ብር በላይ የሚያስቀር ነው፡፡
የበለፀገው ሶፍትዌር (አውቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም) ምን ምን ተግባራትን ያከናውናል? አውቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም የሚያከናውናቸው ተግባራትና ፋይዳው
• የትራፊክ ቅጣት መቀበል፣
• ሪከርድ መያዝ
• ተፈላጊ ሰሌዳ መሥራት
• የአሽከርካሪን አጠቃላይ መረጃ ከዋናው ሰርቨር በመመልከት ውሳኔ መስጠት፣
• የባለሙያዎችን የቀን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሪፖርት ማሳየት
• በከተማ ውስጥ ምን ያህል ሰው እንደተቀጣ/ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ የበላይ አመራሩ የ24 ሰዓት ሪፖርት ማየት እንዲችል ያደርጋል
• ተቆጣጣሪዎች የመደብ ቦታ ላይ ስለመሆናቸው በቀላሉ መቆጣጠር ያስችላል
• ሳይከፈል የሚቀር ቅጣት አለመኖሩ
• ፎርጅድ ቦሎ መቆጣጠር መቻሉ
• ለደረሰኝ የሚወጣ ወጪ ማስቀረቱ
• የገቢ ሪፖርት በቀላሉ መሥራት መቻሉ
• የተቆጣጣሪን የሥራ ጫና ማስቀረቱ
• የሚጠፋ ሰሌዳ/መንጃ ፍቃድ ማስቀረቱ
• የተቆጣጣሪ የሥራ ጫና መቀነሱ
• ሕግ አስከባሪን ጥሶ የሚሄድ አሽከርካሪ ታርጋው ፑሽ በተን ላይ ተፅፎ ከተነካ በአንድ ጊዜ ሁሉም ተቆጣጣሪ ጋር ስለሚደርስ ትዕዛዝ ጥሶ የሚሄድ አሽከርካሪ የለም
• የፓርኪንግ ገቢን ለመቆጣጠር
• ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ ማኅበራትን መከላከል
• ሁሉም የፓርኪንግ ማኅበራትን ወደ ሕጋዊ አሠራር ማምጣት
• በቀን /በሳምንት/ በወር የፓርኪንግ መረጃን ማግኘት
• ሳይከፍሉ የሚሄዱ አሽከርካሪዎችን መከላከል
• አሽከርካሪዎች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ቅድመ መረጃ (የተያዘ/ ያልተያዘ የፓርኪንግ ቦታ) ማግኘት መቻላቸው

አውቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተም ከሁሉም የክፍያ አማራጮች ጋር መናበብ ይችላል፤ በመሆኑም ደንበኞች በእጅ ስልካቸው ጭምር በተቀጡበት ቦታ ላይ ሆነው ቅጣታቸውን መክፈል ይችላሉ። የቅጣት ሪፖርት ያወጣል፤ የፓርኪንግ ክፍያዎችን ያሰላል፣ ያሳውቃል፤ ስለዚህ ደንበኞች ክፍያውን በእጅ ስልካቸው በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ቦታ ላይ ሆነው መክፈል ይችላሉ
ይህ አዲስ ዲጂታል የትራፊክ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ከአዲስ አበባ ሹፌር እና የተሽከርካሪ ፈቃድ (DVLCA) መረጃ ጋር የተዋሐደ ሲሆን፣ አገልግሎት ወይም ቅጣት ሲቀበላቸው ተሽከርካሪዎችን በራሱ ይመዘግባል።
በተጨማሪም የእጅ ክፍያዎችን ለማስወገድና ሕገ-ወጥ የመኪና ማቆሚያዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዲጂታል የመኪና ማቆሚያ መሳሪያ ይዟል።
ቴክኖሎጂው የቆሙ ተሽከርካሪዎችን ይመዘግባል፣ ክፍያ ያሰላል እንዲሁም ክፍያዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ያከናውናል።
የበለፀገውን ሶፍትዌር (አውቶማቲክ ኢንፎርስመንት ሲስተምን) ወደሥራ ለማስገባት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በቅርቡ ምን አከናወነ? የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ከኢንፍራቴክ የመተግበሪያ አምራች የግል ድርጅት ጋር በመሆን ለ11ዱም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና ከማዕከል ለተውጣጡ 700 የቁጥጥር ሠራተኞች በትራፊክ ደንብ ቁጥጥር እና በፓርኪንግ አስተዳደር ሥርዓት መተግበሪያ አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል ፡፡፡