• ወጣቱ ለ158 ሠዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል
“አባትና እናቴ አርሶ አደር ስለነበሩ እነሱ የሚሰሩትን ስራ እያየሁ ነው ያደኩት። ከህፃንነቴ ጀምሮ ወላጆቼ የሚከውኑትን እመለከትና አብሬም የእርሻ ስራ እሰራ ስለነበር እንደ ቤተሰቦቼ የመሆን ፍላጎቴ በአእምሮዬ ተቀርፆ ቀረ፡፡” ይላል ትውልድና እድገቱ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት መከታው ፍቅሬ፡፡
መከታው በመንግስት የብድር አገልግሎት በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ነበር ወደ ከተማ ግብርና ስራ የተሰማራው፡፡ በ2006 ዓ.ም በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከቤተሰብ ጋር በመሆን ስራ ጀመረ፡፡ ከሚያመርታቸው የጓሮ አትክልቶች ጥቅል ጎመን፣ አበባ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ሰላጣ፣ ኪያር፣ ዝኩኒ በተጨማሪም ሙዝ፣ ፕሪም፣ በቆሎ፣ ባቄላ በማምረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ የገበያ ማዕከል ያቀርባል፡፡ ለቸርቻሪዎች ደግሞ ቀጥታ ከማሳ ላይ ንፁህ የግብርና ምርት ይገዛሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች ከደረሱ በኋላ ካልተሸጡ የመበላሸት እድል ስላላቸው ኪሳራ ቢያጋጥም እንኳን በዓመት እስከ 200 ሺህ፣ ኪሳራ ከሌለው ደግሞ እስከ አንድ ሚሊዮን ትርፍ እንደሚያስገኝ ተናግሯል፡፡
ወጣት መከታው የከተማ ግብርና ስራውን በማስፋት በሁለት ቀፎዎች የንብ ማነብ ስራንም በ2014 ዓ.ም ጀመረ፡፡ በዘመናዊ የንብ ቀፎና የንብ ማር ማራገፊያ ማሽን በመጠቀም በዓመት ሶስት ጊዜ የማር ምርት ይገኛል። በአንድ ቀፎ 25 ኪሎ ማር የሚገኝ ሲሆን በዓመት ከአምስት ቀፎዎች 375 ኪሎ ግራም ማር ይመረታል፡፡ አንድ ኪሎ ግራም ንፁህ ማር በ500 ብር ለማህበረሰቡ እያቀረበ ነው። በአሁኑ ወቅትም ሶስት ዘመናዊ ቀፎዎችን በመጨመር ምርቱን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በማምረት ሌላ ቦታ አምስት ሺህ ብር የሚሸጠውን ለአርሶ አደሮች በአራት ሺህ ብር ለሽያጭ ያቀርባል፡፡
ታታሪው ወጣት መከታው በዚህ አላበቃም፤ ከቤተሰቦቹና ወንድሞቹ ጋር በመሆንም መንግስት ባመቻቸው እድል ስራውን በማስፋፋት መስከረም 2016 ዓ.ም ደግሞ በወተት ላም እርባታ ስራ በመሰማራት የስራ እድል ሊፈጥር ችሏል፡፡ ከአርሶ አደር ወላጆቹ ባገኛቸው 20 የወተት ላሞች እርባታ በመጀመር በአሁኑ ወቅት 49 የወተት ላሞች ደርሰዋል፡፡ የወተት መሸጫ ሱቅ በመክፈትም በቀን 400 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ አንድ ሊትር ወተት ውጪ ገበያ ላይ እስከ 100 ብር የሚሸጠውን በ70 ብር በመሸጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለወተት ላሞች የመጠጥ ውሃ የሚሆን በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት የወተት ላሞቹ ምርታማ እንዲሆኑ በመንከባከብ፣ ሲታመሙ በማሳከም ውጤታማ ስራ እየሠራ መሆኑን አርሶ አደር መከታው ተናግሯል፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ 150፣ በወተት ላም እርባታ 6፣ በንብ ማነቡ 2 በአጠቃላይ ለ158 ወገኖች የስራ እድል መፍጠሩን በመግለጽ የተጀመሩትን የከተማ ግብርና ስራዎች ይበልጥ ማሳደጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚገልጸው አርሶ አደሩ፣ ለዚህም የንብ ማር ማራገፊያ እና የወተት ማለቢያ ማሽኖችን ለመግዛት፣ የስጋ ከብት እንዲሁም በግና ፍየል ለማድለብ፣ የዶሮ እርባታ ስራ ላይ ለመሰማራት ሰፊ እቅድ መያዙን ተናግሯል፡፡
መኖሪያ ቤት፣ ሁለት አይሱዙ መኪና፣ አንድ ፒክ አፕ መኪና፣ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የወተት ላሞች ጨምሮ በገንዘብ ቢተመን ወደ 67 ሚሊዮን ብር ካፒታል አፍርቷል፡፡ ይህ ጥሪት የኔ ብቻ አይደለም። የወላጆቼ፤ የወንድሞቼ ጭምርም ነው የሚለው ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆነው ወጣት መከታው ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ የባለቤቱ፣ ወላጆቹና ወንድሞቹ ድጋፍ እንዳልተለየው በመግለፅ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
“መንግስት የብድር አገልግሎት አግኝቼ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ ከራሴ አልፌ ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ አድል እንድፈጥር አስችሎኛል። ወረዳውም ክፍለ ከተማውም በስራዬ ላይ እገዛ አድርጓል። ብድር እንዲመቻች፣ የመሬት ይዞታ ካርታ እንዳገኝ እና ሌሎችም ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ አድርገውልኛል። ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ስላደረጉልኝም አመሰግናለሁ” ብሏል አርሶ አደር መከታው።
አንድ ሰው ትልቅ ደረጃ የሚደርሰውና በተሰማራበት ማንኛውም የስራ መስክ ውጤታማ መሆን የሚችለው አልጋ በአልጋ ሆኖ ሳይሆን ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ነው። ወጣቱም ስራን ሳይንቅ መስራት ይጠበቅበታል ሲል አክሏል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ቡሉላ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ በክፍለ ከተማው በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ 780 አባላት ያላቸው 178 ማህበራት ይገኛሉ፡፡
በከተማ ግብርና ዘርፍ በማህበርም ይሁን በግል ለሚሰሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል። እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ከወለድ ነፃ እንዲያገኙ ይመቻቻል። ካላቸው የመሬት ይዞታ ላይ እንዲጠቀሙ ፍቃድ በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገቡም ድጋፍ ይደረጋል፡፡
በክፍለ ከተማው በከተማ ግብርና በመሰማራታቸው ለአብነት በወተት ላም እርባታ በአምስት የወተት ላም ስራ ጀምረው እስከ አርባ እና ሃምሳ የደረሱ አሉ፡፡ በዶሮ እርባታ ከአንድ መቶና ሁለት መቶ ዶሮ ተነስተው በአሁኑ ወቅት እስከ አስር ሺህ የደረሱ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፎ ለሌሎችም የስራ እድል እየፈጠሩ ያሉበት ሁኔታ እንዳለም ነው ኃላፊው የገለፁት፡፡
በከተማ ግብርና ዘርፍ ተደራጅተው ከሚሰሩት በተጨማሪ ህብረተሰቡ በየቤቱ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ለአብነት “የዶሮ እርባታ ሽታ ያመጣል” የሚሉ በአሁኑ ወቅት አስተሳሰባቸው ተቀይሮ በየቤቱ አምስት አምስት ዶሮ እያረቡና የእለት ፍጆታቸውንም በራሳቸው እየሸፈኑ ያሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አቶ ሙላት አመላክተዋል። ጡረታ የወጡ፣ ቤት የተቀመጡ ግለሰቦችም በግቢያቸው ባለው ቦታ በመስራት ከአምስት ዶሮ ተነስተው እስከ አምስት መቶ እና አንድ ሺህ የደረሱ አሉ። ዘርፉ ስራ ለሌላቸው የስራ እድል ከመፍጠር አንፃርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህ ሌሎች ተሞክሮ በመውሰድ በከተማ ግብርና ወጪያቸውን መሸፈን የሚችሉበትን እድል መጠቀም አለባቸው ብለዋል፤ አቶ ሙላት።
አቶ ሙላት እንደገለፁት፤ በክፍለ ከተማው በከተማ ግብርና ዘርፍ ተሞክሮዎችን ለሌሎች የማስፋት ስራም ተሰርቷል፡፡ ለአብነት ከባህር ዳር፣ ከሃዋሳ በመምጣት ተሞክሮ ወስደዋል፡፡ አርሶ አደሮችም እርስ በርስ በከተማ ግብርናው ዘርፍ ተሞክሮ ይለዋወጣሉ። ጽህፈት ቤቱም አጫጭር ስልጠና ይሰጣል። የእንስሳት ህክምና መድሃኒት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ መኖ እንዲያገኙ ትስስር የመፍጠር ስራም አንዱ ነው፡፡ ከሆቴሎች፣ ፕሮግራም ከሚያዘጋጁ ግለሰቦች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉና ውጤታማ እንዲሆኑ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ነው የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የገለፁት፡፡
ዘርፉ በከተማዋ ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል፣ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሙላት አስረድተዋል፡፡
ተሞክሮዎች እንዲሰፉ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ በፍቃዱ ሰለሞን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ለከተማ ግብርና ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዘርፉ በርካቶች ሀብት አፍርተዋል። ለወገኖቻቸው የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ለከተማው ማህበረሰብም የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ያነሳሉ፡፡
አቶ በፍቃዱ እንደገለፁት፣ የከተማ ግብርና ሲባል አምራቾች ብቻ ሳይሆኑ እሴት በመጨመር እና የተለያየ ግብአት በማቅረብ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ያካትታል። እነዚህ አካላት ጥራቱን የጠበቀ ግብአት ማቅረብ እንዲችሉ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ስራ ይከናወናል፡፡ ይህም በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት አስተማማኝ ግብአት እንዲያገኙ፣ ደረጃቸውንና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት የሚያስችል ነው፡፡
በዘርፍ አስቀድመው የተሰማሩት ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ድጋፎችን እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አቶ በፍቃዱ ያነሳሉ። አንደኛ በከተማ ግብርና የተሰማሩ አካላት ምርትና አገልግሎት ገበያ እንዲያገኝ የገበያ ትስስር መፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ በወተት ላም እርባታ ላይ ለተሰማሩት የተሻሻለ የወተት ላም ዝርያዎችን እንዲያገኙ የማዳቀልና የእንስሳት ጤና ህክምና አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ መኖ በማቀነባበር፣ የአንድ ቀን ጫጩት በመውሰድ በቄብ ደረጃ በማሳደግና ግብአቶችን በማምረት የሚሳተፉት ደግሞ በቤተሰብና በተቋም ደረጃ የከተማ ግብርና ላይ ከተሰማሩ ጋር እንዲተሳሰሩ ይደረጋል፡፡
እንደ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌ፣ የካ፣ ለሚ ኩራና አቃቂ ቃሊቲ ባሉ ማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች መሬትና ልምድም ያላቸው አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች በከተማው ግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ መድረክ በማዘጋጀት እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡ ተደርጓል። አርሶ አደሮቹ ከራሳቸው ባለፈ ለከተማው ነዋሪው የወተት፣ አትክልት፣ እንቁላል፣ የዶሮ ስጋ የማቅረብ አቅም እንዳላቸው ታይቷል፡፡ ጎን ለጎንም በአነስተኛ ከተማ ግብርና ለተሰማሩት መኖ በማቅረብ፣ በዶሮ እርባታ ለሚሰሩት ጫጩት፣ የወተት ላም እርባታ ላይ ለሚሰማሩት ጊደርና የወተት ላሞችን በማቅረብ እንደ ግብአት ምንጭ በመሆን እያገዙ ይገኛሉ፡፡ ኮሚሽኑ አነስተኛ እና በስፋት የከተማ ግብርና ላይ የተሰማሩ አካላት እርስበርስ ልምድ እንዲለዋወጡና እንዲተሳሰሩ በማድረግ ተሞክሮዎች እንዲሰፉ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ በፍቃዱ ያስረዳሉ፡፡
የከተማ ግብርና ስራው ውጤታማ እንዲሆን ሌላኛው የከተማ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በወረዳ ደረጃ የዶሮ እርባታ ዘርፍ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ ባለሙያ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት የዶሮ እርባታ በሰፊው እየተሰራበት የሚገኝ ሲሆን በማሻሻያው ባለሙያዎች እንዲመደቡ ስለተፈቀደ የማሟላት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ በፍቃዱ ነግረውናል፡፡
ከምርምር ተቋማት የሚወጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲጠቀሙ ማስተዋወቅና ማስተሳሰር ሌላው በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ የሚያደርገው ድጋፍ እንደሆነ አቶ በፍቃዱ ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ በቤተሰብና መለስተኛ ደረጃ የሚሰራው የዶሮ እርባታ በሰፊውና በኢንዱስትሪ ደረጃ እንዲከናወን የዘርፉ ተሳታፊዎች ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በማዳቀል አገልግሎትም የወተት ከብት እርባታ ላይ ለተሰማሩት የሚፈልጉትን ሴት ጥጆችን ብቻ የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ በፍቃዱ ይገልፃሉ።
በ2017 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ባዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር በከተማዋ በከተማ ግብርና ተሰርማርተው ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በከተማ ግብርና ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርቡ አካላትም ተሳትፈው ስለነበር እርስ በርስ ልምምድ የተለዋወጡበትና የተማማሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር በመሆን በጳጉሜ ቀናት ኤግዚቢሽንና ባዛር በማዘጋጀት የግብርና ምርት አምራቾችን በማሳተፍ እርስ በርስ ልምድ እንዲለዋወጡና ከሸማቹም ጋር ቀጥታ እንዲገናኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፤ ማህበረሰቡም ምርቶቻቸውን የመግዛት አቅም እንዳለውና የበለጠ ቢሰራ በዘርፉ ካለውም በላይ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል መረዳት መቻላቸውን አቶ በፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀትም በተመረጡ የሀገራችን ከተሞች የግብርና ግብርና ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በአዲስ አበባ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ያገኙትን ጎብኝተዋል፤ እርስ በርስም ልምድ ልውውጥ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በጥቅሉ በአዲስ አበባ ለከተማ ግብርናው በተሰጠው ትኩረት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የስራ ዕድልን በመፍጠር፣ ገበያን በማረጋጋት ውጤት እየተገኘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀም ምርጥ ተሞክሮዎችን ማስፋትና ከባለድርሻ አካላት ጋርም ተቀናጅቶ መስራት ይገባል እንላለን፡፡
የከተማ ግብርና ከራስ አልፎ ለሌሎችም እንደሚተርፍ የሁለገቡ ወጣት መከታው ፍቅሬ ስኬት ማሳያ ነው፡፡ ሌሎችም ከእነዚህ ዓይነት ወጣቶች ውጤታማ ተሞክሮን በመውሰድ በከተማ ግብርና ዘርፍ ቢሰማሩ ከራሳቸው አልፈው ለወገንና ለሀገር የሚጠቅሙ ይሆናሉ መልዕክታችን ነው፡፡
በሰገነት አስማማው