የከተማ ግብርናው የዕውቀትና የውጤት አምባ

አቶ ሰለሞን ሞገስ እና አቶ መንግስቱ ፉፋ በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የጥበቃ ሰራተኞች ናቸው፡፡ የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በምሳሌነትም ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ቀን ከሌሊት ከፍተኛ ንቃትንና ትጋትን በሚጠይቀው የጥበቃ ሥራ በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። ሥራው በፈረቃ እየተተካኩ የሚሠራ በመሆኑ፤ የሚያገኙትን የእረፍት ጊዜ በሌላ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ በማዋል ኢኮኖሚያቸውን ሲደጉሙ ቆይተዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በኮሌጁ የተጀመረው የከተማ ግብርና እነዚህ ታታሪና ምስጉን የጥበቃ ሠራተኞች የእረፍት ጊዜያቸውን በጓሮ አትክልት ልማት ላይ የሚያውሉበትን ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በቡድን በቡድን ተደራጅተው በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተሰጣቸው የልማት ቦታ ላይ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ እስከማቅረብ መድረሳቸውንም ይናገራሉ።

በኮሌጁ እየተስፋፋ ያለው የወተት ላሞች እርባታ

ከልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የከተማ ግብርና ልማት ሥራ ትሩፋት እየተቋደሱ ያሉት አቶ ሰለሞን እና አቶ መንግስቱ ብቻ አይደሉም። የኮሌጁ ሠራተኞች እና የአካባቢው ማህበረሰብም ከልማቱ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። በተለይ አነስተኛ ወርሃዊ ደምወዝ ያላቸው ሠራተኞች በቅጥር ግቢው ባለው ውስን ቦታ ላይ ውጤታማ የከተማ ግብርና ልማት በማከናወን ገቢያቸውን የሚደጉሙበት ሁኔታ ስለመመቻቸቱ የሕንፃ አስተዳደር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አቡሸት ጫኔ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው በሚመሩት ጽህፈት ቤት ውስጥ በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ወርሃዊ ደምወዝ ባላቸው የሥራ መስኮች (ጥበቃ፣ ፅዳት፣ መልዕክት፣ አትክልተኛ እና የጉልበት ሠራተኛ) ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ እነዚህ ሠራተኞች በሚያገኙት ወርሃዊ ደምወዝ ብቻ ኑሯቸውን ለመምራት እየከበዳቸው መምጣቱን አስታውሰዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት እንደ ተቋም ከተወሰዱ መፍትሄዎች መካከል ቁጥራቸው 35 የሚደርሱ ሠራተኞችን በማደራጀት በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ ቦታ ላይ የከተማ ግብርና ልማት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ዝግጅት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የተደረገበት ተግባር ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሕንፃ አስተዳደር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊው አክለው እንዳብራሩት፤ ኮሌጁ ከ30 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የሚሆን ይዞታ አለው፡፡ ይዞታው ላይ 23 ሕንፃዎች ተገንብተው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የትምህርት እና ሥልጠናውን ሥራ የሚያግዙ እና ለተያያዥ ተግባር የሚውሉ መሰረተ ልማቶችም የቅጥረ ግቢው አንድ አካል ናቸው፡፡ በአንፃራዊነት አገልግሎት ሳይሰጡ ወይም ለተረፈ ምርት እና ቆሻሻ ማከማቻ የዋሉ ወይም አረምና ቁጥቋጦ የበቀለባቸው መጠናቸው ቀላል ያልሆነ ቦታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ቦታዎች ነው በከተማ ግብርና ወደ ልማት መቀየር እና ብዙዎችን መጥቀም የተቻለው፡፡ በ2017 በጀት ዓመትምያለውን ክፍት ቦታ አሟጥጦ ወደ ከተማ ግብርና ልማት ለማስገባት በትኩረት ይሠራል።

በከተማ ግብርና ልማት ሥራ ላይ ከተሠማሩ ነባር የተቋሙ ሠራተኞች በተጨማሪ፤ አስር የአትክልተኛ እና የጉልበት ሠራተኞችን በኮንትራት ቀጥሮ ወደ ሥራ ለማስገባት ሂደትተጀምሯል፡፡ ቅጥሩም በቅርቡ የሚጠናቀቅ እና ሥራ የሚጀመር ይሆናል፡፡ አሠልጣኝ ኪዳነወርቅ መላኩ በኮሌጁ ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ዛሬም

በአውቶሜካኒክ የስልጠና ዘርፍ በአሰልጣኝነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜያቸውንበኮሌጁ እንደማሳለፋቸው መጠን ቅጥር ግቢውን የቤታቸውን ያህል ያውቁታል፡፡ አሁን ላይ በከተማ ግብርና ልማት እንቅስቃሴው የተሻለ ውጤት እያመጣ ስላለው ተቋማቸው የቀደመ ገፅታ ከዛሬው ጋር በማነፃፀር፤ “በኮሌጁ የከተማ ግብርና ትምህርት ክፍል ከመቋቋሙ በፊት፤ አሁን ላይ ለተለያዩ የዕፅዋት ልማት እና የእንስሳት እርባታ አገልግሎት የዋሉ ቦታዎች አገልግሎት አይሰጡም፣ በጣም የቆሸሹ እና የግቢውን ገፅታም ያበላሹ ነበር፡፡ እነዚያን ቦታዎች ነው የከተማ ግብርና ሥልጠና ክፍል አሠልጣኞች እና አመራሮች በመነጋገር እና ወደ ተግባር በመግባት ለልማት ያዋሏቸው” ሲሉ ገልፀውታል፡፡

በኮሌጁ የለማ የሙዝ ተክል

የአውቶሜካኒክ አሰልጠኙ አክለው እንዳብራሩት፤ አሠልጣኞቹ ቦታዎቹን አመቻችተው ወደ ልማት ከማስገባት በተጓዳኝ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የተቋሙን ሠራተኞች አስፈላጊውን ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት እና በመደገፍ በጓሮ አትክልት ልማት ላይ እንዲሠማሩ ያስቻሉበት ተግባር የሚደነቅ ነው። የጓሮ አትክልት ልማቱ ሳይንሳዊ ዕውቀት እና ክህሎት ባላቸው አሠልጣኞች ያልተቋረጠ ክትትል እና ድጋፍ የሚደረግለት በመሆኑ፤ በልማት ሂደት ላይ ለሚከሰቱ አረሞች፣ በሽታዎች ወይም ተያያዥ ችግሮች አፋጣኝ እና ተገቢ መፍትሄ የሚሰጥበት ዕድል ሰፊ ነው። ለዚህም ነው ሥራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማሳየት የቻለው፡፡ የከተማ ግብርና ሥራው ለምግብነት የሚውሉ ትኩስ ግብርና ውጤቶችን ከማምረት በተጨማሪ፤ የኮሌጁን ቅጥረ ግቢ አረንጓዴ እና ፅዱ ገፅታ አላብሶታል። ለተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎች የሚመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ሥራውን በአካል ተገኝተው የሚያዩበት እና በቤታቸው የሚተገብሩበትን መነሳሳት ይፈጥራል፡፡

ኮሌጁ በቅጥረ ግቢው ውስጥ ውጤታማ የሆነ የከተማ ግብርና ሥራን እንዲያከናውን ካሉት የሥልጠና ክፍሎች (ዲፓርትመንት) አንዱ የሆነው የከተማ ግብርና ሥልጠና ክፍል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በእርግጥ የሥልጠና ክፍሉ ይህንን እንዲያደርግ የተቋቋመበት ዓላማ እና የሥራው ባህርይ ያስገድደዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ከተማ ግብርና ስልጠና ዘርፍ የዕፅዋት ሣይንስ አሰልጣኝ ይርጋለም አሰፋም የስልጠና ክፍሉ በከተማ ግብርና ዘርፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር እና ትሩፋቱን በልማት ቦታዎቹ በመንቀሳቀስና በማስጎብኘት ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡ “የስልጠና ክፍሉ በኮሌጁ ውስጥ በተለያዩ የከተማ ግብርና መስኮች አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሥራው በዋናነት በስልጠና ክፍሉ ባሉ አሠልጣኞች እና አመራሮች የሚመራ ሲሆን፤ የኮሌጁ አጠቃላይ ማህበረሰብ በተለያየ ሁኔታ ይሳተፍበታል፡፡

በውጤቱም እየተጠቀመ ይገኛል” የሚሉት የዕፅዋት ሣይንስ አሰልጣኝ ይርጋለም፤ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወይም ወርሃዊ ደምወዛቸው በአንፃራዊነት አነስተኛ ለሆኑት የኮሌጁ ሠራተኞች የጓሮ አትክልቶችን አልምተው የሚጠቀሙበትን ቦታ በመስጠት፣ ሙያዊ ስልጠና፣ የዘር አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ በምርቱ የሚጠቀሙበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ቆስጣ የመሳሰሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ከራሳቸው የምግብፍጆታ አልፎ፤ ለተቋሙ ሠራተኞች እና ለአካባቢው ማህበረሰብ በሽያጭ በማቅረብ ኢኮኖሚያቸውን እስከመደጎም የደረሱ አሉ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያለውን ክፍት ቦታ አሟጥጦ ለመጠቀም በኮሌጁ እየተተገበረ ያለው አካሄድ የሚደነቅ ነው።

በኮሌጁ ያለ የቡና ተክል

የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ በመዲናዋ ካሉ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አንፃር በይዞታው ስፋት ሲታይ አነስተኛ (ጠባብ) የሚባል ነው፡፡ ይህም ሆኖ፤ በባህሪው በጠባብ ወይም በአነስተኛ ቦታ ላይ በመተግበር ከፍተኛ የምርትና ምርታማነትን ውጤት በማምጣት የሚታወቀውን የከተማ ግብርና ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መልኩ ከመከወን አላገደውም። የኮሌጁ አሠልጣኞች ለሠልጣኞቻቸው በተግባር የተደገፈ ሥልጠና የሚሰጡባቸው የሠርቶ ማሳያ ቦታዎች በአግባቡ ተዘጋጅተዋል፡፡ በቅጥረ ግቢው የሙዝ እና የአቮካዶ ዕፅዋቶች በስፋት ይገኛሉ። ሙዙ ፍሬውን መስጠት ከጀመረ ሰነባብቷል። በአትክልት እና ዕፅዋት ልምላሜ በተላበሰ ፍሬያማ እና ውብ ሥፍራ ውስጥ በተመቻቸ ቦታ ላይ የተቀመጠ የንብ ቀፎ አለ፡፡ በቀፎውም ታታሪዎቹ ንቦች ረቂቅ እና ድንቅ ሥራቸውንይከውናሉ፡፡ ማሩንም ያሰናዳሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በወተት ምርታቸው የተመረጡ የላም ዝርያዎች በኮሌጁ በተዘጋጀላቸው በረትአስፋላጊው እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ኮሌጁ የእንስሳት እርባታ ተግባሩን አንድ ብሎ የጀመረው በሁለት ላሞች ነበር። እነዚህ ላሞች ሳይንሳዊ መንገድን በተከተለ አግባብ በማራባት አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ ሥምንት ከፍ ብሏል፡፡ እኛ በኮሌጁ በተገኘንበት ወቅት ሦስት ላሞች እርጉዝ መሆናቸውን በባለሙያዎች ተነግሮናል። ወተትን ከሚሰጡት ላሞች የግቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ሆኗል። ላሞች ወተት በሚሰጡበት ወቅት ኮሌጁ ለግቢው ማህበረሰብ አንድ ሊትር ወተት በ15 ብር ያቀርባል። ይህ ለሠራተኛው ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ በቀጣይ የእንሰሳት ሃብት ልማቱ እየተስፋፋ ስለሚሄድ ከተቋሙ ሠራተኛ በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ ከእንሰሳት ተዋፅኦ ምርት የሚጠቀምበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በኮሌጁ የከተማ ግብርና ስልጠና ክፍል ተጠሪ አቶ መለሰ ዘውዴ ስለ ስልጠና ክፍሉ ምስረታ፣ የሠሯቸው ሥራዎች እና በቀጣይ ስላለው ዕቅድ አስመልክተው እንዳብራሩት፤ የከተማ ግብርና የሥልጠና ክፍል በኮሌጁ ስር ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው በ2005 ዓ.ም. ነው። በወቅቱ የሥልጠና ክፍሉ ዋና ትኩረት የወተት ላሞች እርባታ፣ የንብ ማነብ፣ የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት ልማት እና አካባቢን ማስዋብ ዋና ዋና የሥልጠናው የሙያ ዘርፎች ሲሆኑ፤ ሥልጠናዎቹ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በአጫጭር የጊዜ መርሃ ግብር የሚሰጡ ነበሩ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ በአማካይ በዓመት እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ሠልጣኞች ከኮሌጁ መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት ጨብጠው ወጥተዋል፡፡ “እንደ አገር ባለፉት አምስት ዓመታት ለከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰጠው ትልቅ ትኩረት ኮሌጁ ለዓመታት ከመጣበት የሥልጠና ሂደት እንዲወጣ እና በተግባር የተደገፈ የሥልጠና አካሄድን እንዲከተል አድርጎታል” ያሉት የሥልጠና ክፍሉ ተጠሪ፤ የተቋሙን የከተማ ግብርና ልማት ፀጋ የመለየት፣ የውስጥ አቅምን የማቀናጀት፣ የሠው ኃይሉን የማስተባበር እና ወደ ተግባራዊ እርምጃ የመግባቱ ወሳኝ ምዕራፍ የተከፈተው በተለይ በአዲስ አበባ ደረጃ የከተማ ግብርና ሥራ በስፋት መከናወን በጀመረበት ጊዜ ነው። ይህም ጅምር በየዓመቱ ውጤታማነቱ እያደገ መምጣት ተችሏል፤ በቀጣይም የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡

በተለይ የወተት ላሞች እና የዶሮ እርባታን በስፋት እና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ሥራው የግብርና ምርቶችን እስከ ማቀነባበርና እሴት መጨመር (አግሮፕሮሰሲንግ) ደረጃ የማድረስን ዓላማ የያዘ መሆኑን እና ይህም እንዲሳካ ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ፣ በዘርፉ ከተሰማሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚችልበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የሥልጠና ክፍል ተጠሪው አክለው እንዳብራሩት፤ በኮሌጁ ካሉ የስልጠና ክፍሎች ጋር በመሆን አዳዲስ እና ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም አሠራሮችን በመተግበር የከተማ ግብርና ልማት ዘርፍ ምሳሌ ለማድረግ ይሠራል፡፡ የእንሰሳቱ እበት፣ የመኖ ትርፍራፊ፣ አገልግሎት የማይሰጡ የዕፅዋት ምርቶች በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የሚወገዱ ተራ ግብዓቶች አይደሉም፡፡ እነዚህ ተረፈ ምርቶች በዕፅዋት ልማት ላይ ወሳኝ ሚና ያለውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት በግብዓትነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

ከወተት ላሞች ማርቢያ ቦታ (በረት) በቅርብ ርቀት ካለ ቦታ ላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮምፖስት) ተሰናድቶ እየተዘጋጀ፤ ለአገልግሎትም እየበቃ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ባዮ ጋዝ የማምረት ውጥንም በኮሌጁ ዕቅድ ተይዟል። ያለውን ውስን ቦታ በማመቻቸት እንሰሳት የማድለብ ሥራንም ለመጀመር ታቅዷል፡፡

እኛም ይህን በተለያዩ የከተማ ግብርና ስራዎች ውጤታማ የሆነ ተግባር ሌሎች ሊቀስሙት እና ወደ ተግባር ሊቀይሩት ይገባል እንላለን፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review