AMN – ታኅሣሥ -2/2017 ዓ.ም
የከተማ ግብርና በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ /ር) በቅርቡ እንዳሳወቁት የከተማ ግብርና የዘርፉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከማጎልበቱ ባሻገር የከተማ ምጣኔ ሃብትና የሥራ ፈጠራን የሚያሳድግ ነው።
ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ለማጎልበት፣የከተማ ልማት ሥራን ለመደገፍና ሸማቹን በቀጥታ ከአምራቹ ጋር ለማገናኘት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳሉት የከተማ ግብርና ከገጠር ብቻ የሚጠበቀውን አነስተኛ ምርቶች ወደ ከተማ እንዲስፋፋ አድርጓል።
በመሆኑም የከተማ ግብርና ስራ ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ በመምጣቱ ትኩረት የተሰጠውና ተፈላጊ የስራ ዘርፍ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።
በሀገሪቱ ቀድሞ ይሰራበት የነበረው የግብርና ፖሊሲ በአብዛኛው ገጠርን ብቻ ማእከል ያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል።
በመሆኑም የከተማ ግብርና በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በተለይም ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ለከተማ ግብርና በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መምጣቱንም ነው ያነሱት።
በዋናነትም ከ2012 ዓም ወዲህ በታየው ተጨባጭ ለውጥም በማሕበረሰቡ ዘንድ የነበረውን አስተሳሰብ የቀየረ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማ ግብርና ስራ የተጀመሩ ስራዎች ሰፊ ለውጥ በማምጣታቸው የምግብ ዋስትና ስራን በማጎልበት በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በእንቁላል፣ዶሮና ሌሎች ግብርና ስራዎች በከተሞች ያለውን አቅርቦት እንዲሻሻል እያደረገ መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዋናነትም የከተማ ግብርና ስራን ይበልጥ ለማሳደግ በእንስሳት መኖ ላይ የተሻሉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ነው ዶክተር ማንደፍሮ የተናገሩት።
እንደ ሀገር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከተማ አቀፍ የግብርና ንቅናቄ በማካሄድ በተለይ በጓሮ አትክልት ልማት በርካታ ተጠቃሚዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ መደረጉ ይታወሳል፡፡