በአገራችን የግብርናን ሥራ ለገጠራማው አካባቢና ለነዋሪው የህብረተሰብ ክፍል የመስጠቱ እሳቤ ከልማድ አልፎ በተግባር የሚገለጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ለወራት የሚዘንብ ዝናብ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት፣ የቀለም እና የክህሎት ትምህርት የቀሰመ ግዙፍ የሠው ሃይል እያለን፤ ባለ ዕምቅ አቅሙ የግብርና ዘርፍ “ከእጅ ወደ አፍ” የሚሉትን ኑሮ በወጉ መሻገር አቅቶት ለረጅም ዘመን ቆይቷል፡፡ በውሃ ላይ የመጠማትን፣ በለም መሬት ላይ የመራብን፣
በእልፍ ፀጋ ላይ የመደህየትን እንቆቅልሽ ለመፍታት በየጊዜው የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም የሚጠበቀውን ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ትኩረት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ከማድረጉም በተጨማሪ፤ ከዚህ ቀደም ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን አማራጮች የመመልከትና በስፋት የመጠቀም ጅምር ታይቷል፡፡ ጅምሩም በውጤት እየታገዘ፣ እየተስፋፋ፣ ባህል ወደ መሆን እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሊጠቀሱ ከሚችሉ መካከል የከተማ ግብርና አንዱ ነው፡፡
የከተማ ግብርና በከተማ ውስጥና በዙሪያው ባለ አነስተኛ ቦታ ለምግብነትና ለሌሎች ጠቀሜታዎች ሊውሉ የሚችሉ እፅዋትን የማልማት፣ እንስሳትን የማርባት፣ የግብርና ምርት ውጤቶችን የማቀነባበር እና ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ሥራን የሚያካትት ነው፡፡ ይህንን ዘርፍ በርካታ የዓለም አገራት ወደማልማትና መጠቀም ውስጥ የገቡት ቀደም ብለው ነው፡፡ እንደ ኢንዶኔዢያ፣ እስራኤልን የመሳሰሉት አገራት ደግሞ ከከተሞቻቸው የሚያመርቱትን የግብርና ምርት ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሌሎች በመሸጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ አማራጭ እስከማድረግም ደርሰዋል፡፡ የኛዋ መዲና አዲስ አበባ ዘግይታም ቢሆን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብታለች። በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የጓሮ አትክልት ልማት ከግለሰብ ሰገነቶች ጀምሮ፣ በማህበረሰቡ ጓሮ፣ በግልና በመንግስት ተቋማት ግቢዎች እንዲሁም በከተማዋ ወሰን ውስጥ ባሉ አነስተኛ እርሻዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል። የዚህ ሰፊ ሥራ ማሳያ ይሆን ዘንድ የአዲስ ልሳን የዝግጅት ክፍልም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በከተማ ግብርና በዋናነት በወተት ላምና በዶሮ እርባታ እንዲሁም በጓሮ አትክልት ልማት ተሰማርተው ራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ግለሰቦችን እና ተጠቃሚ የሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግራለች፡፡
አቶ ታደሰ አቅነዳ በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ልዩ ስሙ ኮሽም ሰፈር በዶሮ እርባታ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ እሳቸው የሥራቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ በዶሮ እርባታ ስራ ከተሰማሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ 500 ዶሮዎችን እያረቡ ሲሆን በቀን 420 እንቁላል ይሰበስባሉ፡፡ ሥራው ኑሯቸውን የተሻለ አድርጎላቸዋል፡፡ ከራሳቸው ተጠቃሚነት ባለፈም የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፤ ገበያን በማረጋጋትም የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ በመኖ መወደድ ምክንያት ለነጋዴም ሆነ ለአካባቢው ማህበረሰብ አሁን ላይ አንድ ዕንቁላልን በ10 ብር በማስረከብ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ዋጋ ከተወሰነ ጊዜ በፊት 7 ብር እንደነበርም ገልጸውልናል፡፡
ታታሪው አርሶ አደር የከተማ ግብርና ፅንሰ ሃሳብን በተግባር በሚገባ እየገለፁ ስለመሆናቸው እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ይመሰክራል፡፡ በእሳቸው የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚባክን ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ቦታ የዶሮዎች ኩስ ለአፈር ማዳበሪያነት ያገለግላል፡፡ ባላቸው አነስተኛ መሬት ላይ ለሚያለሙት የጓሮ አትክልት (እንደ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ጥቅል ጎመን፣ አበባ ጎመን) ከዶሮ ኩስ የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ምርቱም ራሳቸውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ በጓሮ አትክልት ልማቱ በጋ ላይ መስኖ ተጠቅመው በዓመት ሁለት ጊዜ ያመርታሉ። እንዲሁም በበጋ ድንች በሚያመርቱበት ስፍራ ከእሸት በተጨማሪ ለዶሮዎቹ መኖ የሚሆን በቆሎ በጓሯቸው በመዝራት ድርብ ጥቅምን ይቋደሳሉ። በቀጣይም የስጋ ዶሮዎችን ለማርባት አቅደዋል፡፡
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አስራትም እንደ አቶ ታደሰ በተመሳሳይ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከ2ዐ1ዐ ዓ.ም. ጀምሮ በወተት ከብት ልማት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ 19 የወተት ላሞች ያላቸው ሲሆን በቀን 11ዐ ሊትር ወተት ያገኛሉ። በመኖ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ምርቱ አጥጋቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
ወላጆቻቸው ከብትም ያረቡ ነበር። በልጅነታቸው ይህን እያዩ ነው ያደጉት፡፡ አሁን ላይ ያዩትን ነው እየተገበሩ የሚገኙት። ወደ ከተማ ግብርና ከመሰማራታቸው በፊት በንግድ ስራ ላይ ቆይተዋል፡፡ በዚህ በከተማ ግብርና በተለይም በወተት ከብት ልማት መሰማራታቸው ለህጻናት ልጆች ንፁህ ወተት ለማቅረብ እንዳስቻላቸውና ይህም ደስታ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ለ8 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም አክለዋል፡፡
ወተታቸው ንፁህ ከመሆኑ የተነሳ ከሩቅ ቦታ ሁሉ መጥተው ይወስዳሉ። በዘርፉ መሰማራታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማሳደጉም በላይ ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ንጹህ ወተት እንዲያገኝ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረግን ነው የሚሉት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፤ በአሁኑ ወቅት የከብት መኖ ዋጋ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ስራውን ሲንጀምር 18 ብር ይገዛ የነበረው የከብት መኖ አሁን ላይ 55ዐ ብር ደርሷል፡፡ ሆኖም ይህን ጫና ተቋቁመን እየሰራን እና ለተጠቃሚዎችም እያቀረብን ነው፡፡ ገበያ ላይ 1ዐዐ ብር በሊትር የሚሸጠው ወተት እኛ በ9ዐ ብር ነው ለአካባቢው ማህበረሰብና ነጋዴዎች የምንሸጠው፡፡ እኛን ተመራጭ እንድንሆን የሚያደርገን የዋጋው ቅናሽ ብቻም ሳይሆን በዋናነት ንፁህ ወተት ማቅረብ በመቻላችን ነው ብለዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የከብቶች መኖ ውድ ከመሆኑም በላይ አቅርቦቱም የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በእንስሳት እርባታ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የከብት መኖ የሚገዙት ከቸርቻሪ ነጋዴ ነው፡፡ መኖ ቀጥታ ገበሬው ጋር የሚደርስበት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡ አቅርቦቱ ከተመቻቸ ገበያውን በተሻለ ደረጃ ማረጋጋት እንደሚቻልም አክለዋል፡፡
ወይዘሮዋ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚደረግላቸው ድጋፍ እንዳለ አልሸሸጉም፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ወረዳው ክትትልና ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ የእንሰሳት የጤና ባለሙያዎችን በመላክ ስለ ከብቶች ጤና የምክር አገለግሎት ይሰጧቸዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ ንብ ማነብ ላይ ተሰማርተው የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህንንም ስራ ከ1ዐ ዓመታት በፊት ነው የጀመሩት፡፡ ከማር ምርቱ የራሳቸውን ፍላጐት ከማሟላት ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብም ያቀርባሉ፡፡ የቀጣይ እቅዳቸውም ከብቶቹን የማርባትና ንቦችን የማነብ ስራውን በስፋት ማከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ሃብተወልድ የወይዘሮ ኤልሳቤጥ ጐረቤት ናቸው፡፡ እሳቸው ከሚያመርቱት ንፁህ ወተት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ ከሌላው ገበያ በዋጋም በጥራትም የተሻለ ነው፡፡ ማርም ከእሳቸው ገዝተው እንደሚጠቀሙ ነግረውናል፡፡
አቶ ውቤ ዳርጌ በወረዳ 11 የኮሽም ሰፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው በርካታ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ግለሰቦች መኖራቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ “እኔና የአካባቢው ማህበረሰብ ያለምንም መንከራተት ትኩስና ንጹህ ምርት በአቅራቢያችን ማግኘት ችለናል፡፡ በተለይም የጓሮ አትክልቶች እንደ ጎመን፣ ሰላጣና ቆስጣ የመሳሰሉትን ገበያ ርቀን መሄድ ሳያስፈልገን እንድንጠቀም አድርጎናል። በዋጋ ረገድም ቅናሽ ነው፡፡ ዛሬ ገበያ ላይ
የጎመን ዋጋ እንኳን ከፍተኛ ነው፡፡ በትንሹ ከ30 ብር በታች አይገኝም፡፡ እኛ ግን እስከ 10 ብር ገዝተን እንበላለን፡፡ እንቁላል በ7 ብር እንገዛ ነበር” ይላሉ አቶ ውቤ፡፡ እንዲሁም ድንች 10 ኪሎ በሚይዝ ሳህን ከገበሬ በ150 ብር ይገዛሉ፡፡ ካሮት የ10፣ 15 እና 20 ብር በችርቻሮ ይሸጣል፡፡ ይህ በመደብ የሚሸጠው ሲመዘን ከኪሎ በላይ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ የካሮት ዋጋ በኪሎ እስከ 60 እና 70 ብር ነው የሚሸጠው” ብለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመኖ መጨመር ጋር ተያይዞ የተወሰነ ጭማሪ ቢኖረውም ከገበያው ጋር ሲነጻጸር ግን አሁንም የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ውቤ ገለጻ፣ ባለፉት ጊዜያት እንቁላል ገበያ ላይ 14 እና 15 ብር ገብቶ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 10 እና 11 ብር ዝቅ እንዲል ያደረገው የእነዚህ አምራቾች እየተበራከቱ መምጣት ነው፡፡ ገበያ የሚቀርቡት የጓሮ አትክልቶችም ከሩቅ ቦታ በመኪና ተጭነው ብዙ ቀናትን ፈጅተው ትኩስነታቸው ጠፍቶ ጠውልገው ነው የሚደርሱት፡፡ ብዙ ጊዜ ውሀ እየነከሩ ሲሸጡ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ በአካባቢያቸው የሚያገኙት የግብርና ውጤቶች ግን ዋጋቸው ቅናሽ ከመሆኑም በላይ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ጣዕም ያላቸው ትኩስ ምርቶች ናቸው፡፡
በክፍለ ከተማው የወረዳ 11 አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አዱኛ በወረዳው የከተማ ግብርና አተገባርና ለአካባቢው ነዋሪዎች እየሰጠው ስላለው ጠቀሜታ ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል። በገለጻቸውም፤ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ተግባራት ከቤተሰብ የምግብ ፍጆታ ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛል። ተግባራቱ ከግለሰቦች ሰገነቶች ጀምሮ፣ በማህበረሰቡ ጓሮ፣ በግልና በመንግስት ተቋማት ግቢዎች ላይ የተሰሩ ስራዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች ትኩስ ምርትን ከማቅረብ ጎን ለጎን ለአካባቢ ጥበቃ እና ለህብረተሰቡ ማህበራዊ ትስስር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው። አብዛኛው የወረዳው ነዋሪ በከተማ ግብርና የተሰማራ ነው፡፡ በእንስሳት እርባታ ብቻ ከ13ዐ በላይ አርብቶ አደርና አርሶ አደሮች አሉ፡፡
በወተት ላምና በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ 3ዐ እና 4ዐ ላሞች አሏቸው፡፡ በዶሮ እርባታም ከ1ዐዐ በላይ ዶሮዎችን የሚያረቡ 15ዐ የሚሆኑ ተደራጅተው የሚሰሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አሉ፡፡ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት እያንዳንዳቸው 5 እና 1ዐ ዶሮዎች ያላቸው 2ዐዐዐ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፈው ለገበያ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡
በጓሮ አትክልት ዙሪያም በነዋሪዎቹ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ድንች፣ ካሮት፣ ጎመን የመሳሰሉ ይመረታል፡፡ በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ ነዋሪው ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ቀደም ሲል በጠባብ ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልት አይሰራም፡፡ ዶሮ አይረባም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በዕቃ ጭምር በትንሽ ቦታ የጓሮ አትክልት በማምረት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ እያገዛቸው ይገኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት የከተማ ግብርና መስፋፋት ገበያን ከማረጋጋት አንጻር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በ9ዐ ቀናት እቅድ ውስጥ በተደረገው ግምገማ የነዋሪዎችን ገበያ ማረጋጋት የሚቻለው ከመደበኛ ስራ በተጨማሪ የሌማት ትሩፋት ሲተገበር እንደሆነ በመታመኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ይህም በከተማ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ግብርና መስራት አይቻልም የሚባለውን አመለካከት አስቀርቷል፡፡ ብዙ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና ተሰማርተው ህይወታቸውን ለውጠዋል፡፡ የመንግስትን ፖሊሲ በመከተል ገበያን የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ነዋሪዎች ከገበያ ከሚገዙት ይልቅ በአቅራቢያቸው ከሚመረተው የሚገዙት በዋጋም ሆነ በጥራት የተሻለ ነው፡፡ ንፁህ ወተትና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ማግኘት ችለዋል፡፡ ለእንደዚህ አይነቱ ለውጥ የአመራሩ ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው፡፡ በየብሎኩ በመውረድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል፡፡ መጀመሪያ ላይ የነዋሪው አመለካከት ዝቅተኛ ነበር፡፡ በብሎክ 5 ሰዎች ብቻ ነበር የሚሳተፉት፡፡ በሂደት ግን የነዋሪው አመለካከት እያደገ በመምጣቱ አሁን ላይ በአንድ ብሎክ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ናቸው የማይሳተፉት፡፡ አንዱ ከአንዱ እየተማረ እየሰፋ መጥቷል፡፡ የወረዳው አመራርም የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ ለማስፋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከላይ የከተማ ግብርና ተሳታፊዎችንና የምርቱ ተጠቃሚዎችን በማሳያ አነሳን እንጂ በዘርፉ ላይ በንቃት የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥራቸው ከዕለት ተዕለት እየጨመረ እንደመጣ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ መተግበር የጀመረው የከተማ ግብርና ምን ውጤት እንዳመጣ የአርሶአደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሞሽነር አቶ ፋሩቅ ጀማል ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የከተማ ግብርና መተግበር የጀመረው በ2012 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱም 53 ሺህ 54 ሰዎች ናቸው የተሳተፉት፡፡ በሂደት የተጠቃሚው ቁጥር ወደ 456 ሺህ 650 አካባቢ አድጎል፡፡ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 223 ሺህ 775 አዳዲስ ተሳታፊዎች እንዳሉና በአሁኑ ወቅት በድምሩ ከ680 ሺህ 425 ተጠቃሚዎች ተሳትፈዋል፡፡ እነዚህ ተጠቃሚዎች የተሳተፉት በሦስት መንገዶች በተቋም፣ በጓሮ እና በማሳ ነው፡፡ በተቋም ደረጃ 2 ሺህ 327 በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በሌሎች የአስተዳደር ተቋማት የከተማ ግብርና እንዲተገበር ተደርጓል፡፡ በማህበረሰብ ደረጃም በግቢና በጓሮ እንዲሁም በማሳ ደረጃ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የተገኘውን ውጤት አቶ ፋሩቅ ሲያብራሩ፤ ማህበረሰቡ ምግቦችን በግቢውና በጓሮው እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በከተማ ግብርና የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ አይደረግም፡፡ ከዚህ አንጻር ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ ምግብ (Organic Food) የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በተለይም በ2016 ዓ.ም 325 ሚሊየን ሀብት በማንቀሳቀስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ለእያንዳንዳቸው አምስት ዶሮዎች እንዲያገኙ በማድረግ በየቀኑ አምስት እንቁላል እንዲያገኙና በማእዳቸውም እንቁላል እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ ገበያም ላይ በብዛት እንዲገኝ በማድረግ ህብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ላይ ውጤት ያለው ስራ ተሰርቷል፡፡ በወተትም በማር እንዲሁም የተለያዩ አትክልቶችን ከጓሮና በአነስተኛ ዋጋ ከማሳ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው፡፡
ይህ የከተማ ግብርና የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻልና ከባቢን አረንጓዴ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይም ገበያን በማረጋጋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ አቶ ፋሩቅ ሲያብራሩ፣ “በበአላት ወቅት በገና፣ ፋሲካ… ሽንኩርት 150 ብር ገብቶ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከ100 ሄክታር በላይ የሽንኩርት ምርት ነበር፡፡ ምርቱንም የእሁድ ገበያን ጨምሮ በተለያዩ የገበያ አማራጮች እንደ ባዛርና የአርሶአደር ማሳዎች በ55 ብር ህብረተሰቡ ገዝቶ እንዲጠቀም ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ የቲማቲም ምርትም በብዛት ስለነበረ 20 ብር እንዲሸጥ ተደርጓል፡፡ እንቁላልም ገበያ ላይ 16 ብር በሚሸጥበት ወቅትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንሰሳት ልማት ልህቀት ማዕከል 8 ብር ማቅረብ ተችሏል፡፡ የወተት ዋጋም 140 ብር ደርሶ በነበረበት ወቅት በማእከሉ 70 ብር እንዲሸጥ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ ዶሮ ገበያ ላይ ከ1 ሺህ በላይ የነበረውን ከ3 መቶ 50 እስከ 500 ብር ማቅረብ ሲጀመር አጠቃላይ የዶሮ ዋጋውን ወደ 500 ብር እንዲወርድ አደረገው፡፡ በዚህም ከ20 እስከ 28 በመቶ የከተማውን ገበያ ማረጋጋት ተችሏል፡፡ በየቦታው የተከማቸው ምርት ወደ ገበያ እንዲወጣ ጫና በመፍጠር ገበያው እንዲረጋጋ የጎላ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል፡፡
በእንስሳት እርባታ ላይ የተሳተፉ አካላት ከእንስሳት መኖ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ላነሱት ጥያቄ ምክትል ኮሞሽነር አቶ ፋሩቅ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሻቸውም፤ ጥያቄያቸው ትክክል ነው፡፡ የእንስሳት መኖ ዋጋ ሊጨምር የቻለው ከፋብሪካ የሚወስዱት የመኖ ዋጋ በኩንታል 450 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ስለተጨመረበት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ግብርና ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ተነጋግረው መፍትሄ እንዲያመጡ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ከፋብሪካ ከሚገኝ መኖ ውጪ እንስሳት አርቢዎች ባላቸው ውስን ቦታም ቢሆን መኖ በራሳቸው ማምረት እንዲችሉ ስልጠና የመስጠትና የማረታታት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመዲናዋ የመኖ ፋብሪካ እንዲቋቋም ኮሚሽኑ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
እኛም ይህ ኑሮን በማረጋጋት ረገድ አይተኬ ሚና ያለው የከተማ ግብርና ስራ ከዚህም በላይ እንዲጠናከር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡
በለይላ መሃመድ