AMN-ጥር 7/2017 ዓ.ም
የ2017 ዓ/ም የከተራና የጥምቀት በዓል የጥበቃ ስምሪትን አስመልክቶ በወጣ ዕቅድ ላይ ጥምር የፀጥታ አካላት ውይይት አደረጉ፡፡
የ2017 ዓ/ም የከተራ እና የጥምቀት በዓላትን አስመልክቶ በተደረገው ውይይት ላይ ጥምር የፀጥታና ደህንነት አካላት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ውይይቱን የመሩትና የስራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡
በዓላቱ በስኬት እንዲከበር ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርና በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የስምሪት አቅጣጫን በመከተል ፀጥታ የማስከበር ተግባሩ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ ስርዓት እንዲከበር ከኃይማኖት አባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውጤታማ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
የበዓሉን ድምቀት ሊያበላሽ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ህገ-ወጥ ድርጊትና እንቅስቃሴን የፀጥታ ኃይሉ እንደማይታገስ አስታውቀዋል። ህብረተሰቡንና መላው የፀጥታ መዋቅሩን በተገቢው በማስተባበር በዓሉ በሠላም እንዲከበር አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፣ በከተማዋ የተለያዩ የአደባባይ በዓላት በሠላም መከበራቸውን አስታውሰው የፀጥታ አካላቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር አስቀድሞ በሚደረግ ጠንካራ ዝግጅት የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የ2017 ዓ/ም የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲከበር በዓሉን የሚመጥን ጠንካራ ዝግጅት እንደተደረገ አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከስልሳ በላይ ታቦታቱ የሚያርፉባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ አስታውሰው ጃን-ሜዳን እና አቃቂ ቃሊቲ የታቦት ማደሪያ ቦታን ጨምሮ ህዝብ በብዛት በሚታደምባቸው ባህረ ጥምቀቶች ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ህዝብ በብዛት የሚታደምባቸውን በዓላት እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ከሚያከናውነው ግልፅና ሥውር ጥበቃ ባሻገር ህብረተሰቡ አካባቢውን በመቆጣጠርና መረጃ በመስጠት ተባባሪነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ማሳሰባቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያሳያል፡፡