አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 የኩላሊት ጠጠር ተብለው የሚታወቁት በኩላሊት ውስጥ የሚፈጠሩ ከሚኒራል፣ አሲድ እና ጨው የተሠሩ ጠንካራ የጠጠር ክምችቶች ናቸው።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት፣ አጋላጭ የጤና እክል እና አንዳንድ መድሃኒቶች ከብዙ የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የኩላሊት ጠጠር ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ መቆየት የሚችል የህመም አይነት ሲሆን ፥ ጠጠሩ ከተከሰተ በኋላ ከኩላሊት ተነስቶ በሽንት ማስወገጃ መስመር በኩል በሚያደረገው ጉዞ ህመም ስለሚፈጥር ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
የኩላሊት ጠጠር ከኩላሊት እስከ ፊኛ ድረስ የትኛውንም ክፍል ሊያጠቃ የሚችል ቢሆንም በጊዜ ከታወቀ ጉዳቱ የከፋ እንደማይሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ጠጠሩ ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው ሽንት በሚጠራቀምበት ጊዜ ሲሆን ፥ ይህም ሚኒራሎች እንዲዋሃዱ እና እንዲጣበቁ ያስችላቸዋል፡፡
የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር ለመከላከል የአመጋገብ ለውጥን ጨምሮ መደረግ ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡
እንደአብነት በቀን ውስጥ የሚወስዱትን የፈሳሽ መጠን መጨመር፣ 3 ሊትር ውሃ በመጠጣት የሚያስወግዱት የውኃ ሽንት መጠን 2 ነጥብ 5 ሊትር እንዲሆን ማድረግ፣ የአመጋገብ ባህልን መቀየር ናቸው፡፡
የአመጋገብ ባህልን መቀየር ሲባል የጨው መጠንና የፕሮቲን መጠናቸው የበዛ ምግቦችን ማስወገድ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ ፣ የስጋ ፍጆታን መቀነስ፣ በቂ ካልሽየም ያላቸውን ምግቦች መመገብ ማለት ነው፡፡
ለኩላሊት ጠጠር ተጋላጭነትን በተመለከተም የህክምናው ባለሙያዎች እደሚስማሙት ለኩላሊት ጠጠር ሕመም ተጋላጭ የሚሆኑት በጎልማሳ (40 ዓመትና ከዚያ በላይ)የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሲያጠቃ በአብዛኛው ወንዶች ላይ ይከሰታል፡፡
በተጨማሪም ÷ ከፍተኛ መጠን ያለው የፕሮቲን፣ ጨውና ስኳር መጠን ያላቸው ምግቦች በብዛት መውሰድ፣ በቂ የፈሳሽ መጠን አለመውሰድ ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም ይነሳሉ፡፡
የኩላሊት ጠጠር ሕመም ምልክቶች ናቸው ብለው ባለሙያዎች ከተስማሙበቸው ምልክቶች ውስጥ÷
• ከፍተኛ የጎን የሕመም ስሜት እና ከጎድን አጥንት በታች የጀርባ ሕመም ስሜት፤
• ወደ ንፍፊትና ወደ ታችኛው የሆድ ክፍል የሚሰራጭ ከፍተኛ የሕመም ስሜት
• የውኃ ሽንትን በምናስወግድበት ወቅት የሚኖር ከፍተኛ የሕመም ስሜት፣
• የውኃ ሽንት ቀለም ለውጥ(ቀይ፣ ቡኒ ወይንም ሮዝ)፣
• የደፈረሰ ወይንም መጥፎ ጠረን ያለው የውኃ ሽንት፣
• አጣዳፊ የውኃ ሽንት መኖር፣
• የውኃ ሽንት ከሌላው ጊዜ በተለየ መብዛት፣የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ የህመሙ ምልክቶች ሲሆን በኩላሊት ጠጠር ምክንያት የሚከሰት ሕመም የጠጠሩን እንቅስቃሴ ተከትሎ ቦታውን ሊቀያይር ይችላል፡፡
እነዚህ ምልክቶች የተለመዱ የኩላሊት ጠጠር ምልክቶች ሲሆኑ ፥ ከነበረው በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የሕመም ስሜት የሚሰማዎ ከሆነ፣ ከፍተኛ የየውጋት ስሜት ካለ፣ማቅለሽለሽና ማስመለስ ከተከሰተ፣ ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ካለዎት፣ ደም የቀላቀለ የውኃ ሽንት ሲኖርና ሽንት ማስወገድ ካቃተዎ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ይኖርብዎታል፡፡
የኩላሊት ጠጠር ህክምና ያለው ሲሆን ፥ ሕክምና እንደጠጠሩ ዓይነት እና መጠን እንደሚለያይ ከሄልዝ ላይን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሐኪምዎ ጡንቻዎችን የሚያፍታታ መድኃኒትም በመስጠት ጠጠሩ ከውኃ ሽንት ጋር ተቀላቅሎ እንዲወጣ እንዲረዳዎ ሊያደርግ ይችላል፡፡
የጠጠሩ መጠን ትልቅ ከሆነ ሐኪምዎ የተለያዩ ጠጠሩን የማስወገጃ መንገዶችን የሚያስረዳዎ ስለሚሆን ሐኪምዎን በሚገባ ማማከር ተገቢ ነው፡፡