AMN – ታኀሣሥ 28/2017 ዓ.ም
የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው፣ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ በኃይማኖታዊ አስተምህሮው መሠረት በልደቱ ያገኙትን በረከትና መዳን፣ ትህትናና ፍቅር በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመልዕክታቸው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የጥላቻና ያለመግባባት መንፈስ በፍቅርና በይቅርታ ተቀይሮ ሰውና አምላክ መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደረገ ነው ብለዋል።
ያለፉት ጉዳዮቻችን ክፉውንም ደጉንም አቅፈው የያዙ ቢሆኑም ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን ስለሚበዙ መንግሥት ያመቻቸውን የብሔራዊ ምክክር አጋጣሚዎችን በመጠቀም የሰፉ ልዩነቶችን በመቻቻልና በፍቅር በማጥበብ ዘላቂ አብሮነት ማጠናከር ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።
የገና በዓልን ስናከብር ያለ ልዩነት እርስ በርስ በመተጋገዝና በመደጋገፍ ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ የተቸገሩትን የምንረዳበት፣የታመሙትንና በማረሚያ ቤት ያሉትን በመጠየቅ፣ የተራቡን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣትና የታረዙትን በማልበስ ለፈጣሪና ለወገናችን ያለንን ክብር የምናሳይበት በዓል ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው የገና በዓል የእምነቱ ተከታዮች የእርስ በእርስ ያላቸዉን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክሩበት ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።
ክብረ በዓሉ ሀይማኖታዊ ትዉፊቱን በጠበቀ መልኩ መቻቻልንና መከባበርን ለመላው የዓለም ህዝብ የሚገለፅበት ታላቅ በዓል እንደሆነም አስታውቀዋል።
በዓሉን ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክርና የክልሉን ሰላምና ልማት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ስሜት ማክበር እንደሚገባም መናገራቸውን ከየክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻዉ ጣሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ፤በሁሉም መስክ በሚከናወኑ ስራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ መሆን አለበት ብለዋል።
የተያዘው በጀት አመት በሁሉም ዘርፍ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።