ክረምት ተማሪዎችን ጨምሮ የእረፍት ጊዜ ያላቸው ሰዎች ይህን እረፍታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያግዙ ብዙ አስደሳች፣ አስተማሪ እና ተወዳጅ አማራጮች አሉት። ለቀጣይ አመት የሚረዳ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመማር፣ በቤት ውስጥ ስራ ቤተሰብን ለማገዝ፣ የእግር ኳስ ቡድን አባል ሆኖ ለመጫወትና ለመዝናናት… ተመራጭ ጊዜ ነው። በአጠቃላይ ከመደበኛ ትምህርት እና ስራ ውጭ ያሉ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን እድል ይሰጣል፤ ክረምት፡፡ ለመሆኑ በክረምት እረፍት ላይ የሚሆኑ ሰዎች ጊዜያቸውን በምን ማሳለፍ እና መዝናናት ይችላሉ? ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከክሪምሰን ግሎባል አካዳሚ ባለፈው ዓመት ያጋራውን መረጃና የሀገራችንን ልምዶች በማካተት ስለክረምትና የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ አማራጮች ይህን ጽሁፍ በአጭሩ አዘጋጅቷል፡፡
ቋንቋ መማር
ተማሪዎች ቋንቋን በክፍል ውስጥ ከሚማሩት መደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በእፍት ጊዜያቸው ዘና እያሉ ቢማሩት የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ አዳዲስ ቋንቋዎችን ለመማርም ሆነ የሚያውቁትን ለማሻሻልም ተመራጭ ጊዜ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም በአለም አቀፍ የጥናት መርሃ ግብር ለመሳተፍ ወይም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን ለመማር ከወትሮው በተለየ ክረምትን ቀዳሚ ምርጫቸው እንደሚያደርጉት ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መደበኛ ትምህርት ስለማይኖር እንዲሁም አዲስ ቋንቋ መማር ብዙ ጥቅሞች እንደሚያስገኝ ስለሚረዱ ነው፡፡ ምክንያቱም በሉላዊነት (በግሎባላይዜን) ዓለም ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን በስራው አለምም ተወዳዳሪና ተፈላጊ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ በክረምት ወቅት ለቋንቋ ትምህርት ጊዜ መድቦ ተግባራዊ ማድረግ በተለያዩ መስኮች ስኬታማ የመሆን እድልን ከፍ ያደርጋል፡፡
መክሊትን መፈለግ
በክረምት ተማሪዎች ሙዚቃ ይማራሉ። ሃይማኖታዊ መዝሙር ያጠናሉ፡፡ የስነ ጽሁፍ እውቀትን ይሸምታሉ፡፡ ፊልም እና የትወና ጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ወደ ሲኒማ ቤቶች ሄደው ይለማመዳሉ፤ የፊልም ትምህርት ቤቶችን ይጎበኛሉ፡፡ የስዕል ተሰጥኦ ያላቸው ብሩሽና ሸራን በነጻነት ለማገናኘት ሰፊ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ የፎቶ ግራፍ ዝንባሌ ያላቸው በዘርፉ ይሰማራሉ። ስለዚህ ክረምት ሰዎች ከመክሊታቸው ጋር የሚገናኙበትና የሚተዋወቁበት ጊዜ ነው ይላል የክሪምሰን ግሎባል አካዳሚ መረጃ፡፡
ይህ ሁነት በተለይ ለተማሪዎች የወደፊት ህይወት እና እድገት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ፎቶ ግራፍ ማንሳት፣ የምግብ ሙያ፣ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወትን የመሳሰሉ አዳዲስ የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ተግባራትን መሞከር አዲስ ስሜት እና ልምድን ይፈጥራል። ይህም ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ተማሪዎች ጋር ለመገናኘት፣ ልምድ ለመለዋወጥ እና ወደፊትም የኪነ ጥበብ ማህበር ለመመስረት በር ሊከፍት ይችላል፡፡
የበጎ አድራት ተግባራት ላይ መሳተፍ
ተማሪዎች በክረምት የእረፍት ጊዜያቸው የሚሰሩት የበጎ ፈቃድ ስራ ለማህበረሰቡም ሆነ ለራሳቸው የሚኖረው ዋጋ ብዙ ነው፡፡ ወገናቸውን ከማገልገላቸውም በላይ አዳዲስ ጓደኞችን ያፈራሉ፤ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ የውሎ አማራጮቻቸውን ያሰፋሉ፡፡ በሀገራችንም ተማሪዎች ክረምትን በችግኝ ተከላ፣ በቤት እድሳት፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን በሚያግዙ ተግባራት፣ በክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት እና በሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባር መስኮች ተሰማርተው ያሳልፉታል፡፡ በተጨማሪም በቤተ- መጻሕፍት ውስጥ መፃሕፍትን በማደራጀት፣ በቴክኖሎጂ እንዲጠናከር በማድረግ እና አንባቢዎችን በመርዳት እየተዝናኑ እና እውቀት እያገኙ ሌሎች ሰዎችንና ሀገራቸውን መርዳት ይችላሉ፡፡
ንባብ
በክረምት የእረፍት ጊዜ ባላቸው ተማሪዎችና ሌሎች ሰዎች መደረግ አለባቸው ተብለው ከሚመከሩት ነገሮች ውስጥ ንባብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳን ለማንበብ ወቅት መጠበቅ አስፈላጊ ባይሆንም ክረምት ግን ከቀለም እውቀት ወጣ ያሉ የልብወለድ፣ የፍልስፍና፣ የግጥምና ሌሎችን መፃሕፍት ለማንበብ እድል ይሰጣል፡፡ በሀገራችንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተማሪዎች ወቅቱን በንባብ ያሳልፋሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በክረምት መጽሐፍት እየተዋዋሱ ማንበብን በርካቶች የሚያስታውሱት አስደሳች ትዝታቸው ነው፡፡
በእርግጥ እረፍት የመዝናናት እና የመታደስ ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን እራስን በመፅሐፍ አለም መነጽር ለማየትም ጥሩ አጋጣሚ ነው። የመጽሐፍ ውይይቶች ላይ መሳተፍ፣ የመጽሐፍ ክበብ መመስረት ወይም ስለ ተወዳጅ ልብ ወለድ መወያየት ሰዎችን ሊያቀራርብ እና ትርጉም ያለው ውይይቶችን ሊያሳድግ ይችላል። እንዲሁም ከማያቋርጥ የማህበራዊ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እረፍት ይሰጣል፡፡
ጉብኝት
ክረምት መኖሪያ አካባቢንም ሆነ ራቅ ያሉ ቦታዎችን ወይም አለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከላትን ለመጎብኘት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ካምፓስ ግሩፕ የተሰኘው ገጸ- ድር እ.ኤ.አ በ2018 ክረምትና የእረፍት ጊዜን በሚመለከት ባወጣው መረጃ ላይ እንደጠቀሰው ክረምት በከተማ ውስጥ የእግር ጉዞ ለማድረግ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጎብኘትና ከዚህ በፊት ያላደነቋቸው ታሪካዊ ሙዚየሞችና ስፍራዎች ለመጎብኘትና አይረሴ ጊዜን ለማሳለፍ ተመራጭ ወቅት ነው፡፡ በተጨማሪም ብዙ ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በክረምት ወራት የበለጠ ሰው ስለሚበዛባቸው ከሌሎች ጋር አስደሳችና አዝናኝ ልምድ ለመለዋወጥ ይረዳል። ይህም ተማሪዎች አስተሳሰባቸውን እንዲያሰፉ እና በዙሪያቸው ስላለው ዓለም ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
በጊዜው አማረ