አሁን አሁን በርካታ ዜጎች በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በመሰልጠን የተለያዩ ሙያ ባለቤቶች እየሆኑ ነው፡፡ በሰለጠኑት ሙያ ስራን በመፍጠር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወገኖች የስራ እድል ሲፈጥሩ እና ሀብት ሲያፈሩ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ለእነዚህ ዜጎች በር ከፋች የሆኑ በርካታ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛሉ፡፡ የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ክህሎትና ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ ዜጎች በየመስኩ ለማፍራት አንጋፋው እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል፡፡ በ2017 የትምህርት ዘመንም አዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለማሰልጠን እየተሰናዳ ነው፡፡ የቅድመ ዝግጅት ስራውን አስመልክቶ በኮሌጁ የሬጅስትራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሰልጣኝ ስመኝ ሚደቅሳ ለጋዜጣው ዝግጀት ክፍል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ኮሌጁ በዘንድሮው ዓመት 2 ሺህ 39 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያሰለጥን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ በወረደው እቅድ መሰረት አስፈላጊና ትኩረት የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች ጨምሮ ወደ ተግባር የመቀየር ስራ ይሰራል። ለዚህ ደግሞ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ምዝገባውን ለማካሄድ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ካሉ 5 የመንግስትና 7 የግል ትምህርት ቤቶች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት ተፈጥሮ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

ይህም ወደ ኮሌጁ የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ስለ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ጥሩ መረዳት እንዲኖራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡ ተማሪዎች ከመመዝገባቸው አስቀድሞ በኮሌጁ በሚሰጡ በአስራ አንዱ የትምህርት ዘርፎች ምን አይነት ስልጠና እንደሚካተት፣ በምን መልኩ ስልጠናው እንደሚሰጥ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ በዚህም የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በተለይ በኤስቴቲክስ ዲፓርትመንት ውስጥ ሙዚቃ፣ ቴአትርና ሌሎች የሥነ-ጥበብ ዘርፎች ላይ በከተማ ደረጃ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚሰጠው በኮሌጁ ብቻ በመሆኑ ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ለምዝገባ ቅድመ ዝግጀት ከሁሉም የስልጠና ክፍሎችና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ከመንግስትና ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች ኮሌጁ የሚሰጠውን ስልጠና ተገንዝበው መሰልጠን እንዲችሉ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት በቴሌ ግራም እየተገናኘ የመረጃ ልውውጥ ያደርጋል፡፡ በተቋሙ ገፀ-ድር ምዝገባ እንዲያካሂዱ መረጃ ይተላለፋል፡፡ አዲስ ተማሪዎች መረጃ የሚያገኙበት መንገድም ተፈጥሯል፡፡
የሥልጠና ግብዓት ዝግጅትን በተመለከተ ኃላፊው ሲያስረዱ፤ በኮሌጁ ለየትምህርት ዘርፉ ለተግባር ልምምድ የሚሆኑ አስፈላጊ ማሽኖች ይገኛሉ፡፡ መለዋወጫ የሚያስፈልጋቸው እንዲሟላላቸው እንዲሁም የሚጠገኑ ማሽኖች እንዲጠገኑ ጨረታ በማውጣት ሁሉም ለሰልጣኞች ተግባራዊ ልምምድ ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ኮሌጁ የመማሪያ ክፍል፣ የቤተ መፃህፍት፣ የምድረ ግቢ ማስዋብና ሌሎችንም በመስራት ሰልጣኞችን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡
አሰልጣኝ ስመኝ እንደሚገልፁት፣ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለመማር ማስተማር ሂደቱና ብቁ ሰልጣኞች ለማፍራት ራሱን እየፈተሸ፤ የማሰልጠን አቅሙን እያሳደገ የመጣ ተቋም ነው። ኮሌጁ ብቃት ያላቸው አሰልጣኞችም አሉት፡፡ እያንዳንዱ አሰልጣኝ የሙያ ብቃቱ ተመዝኖ ነው እያሰለጠነ የሚገኘው። ዘንድሮም ስልጣኞችን ለመቀበል በሚደረገው ጥረት ለማሰልጠን ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ ተማሪዎች ምዝገባ ሲጀመር በቅድሚያ በኮሌጁ የሚሰጡ ስልጠናዎች የእያንዳንዱ ዲፓርትመት ሃላፊና ተወካይ ለሰልጣኖች ሙሉ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ተማሪዎች ግንዛቤያቸውን ካሰፉ በኋላ በሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ መርጠው እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ባዘጋጀው ገፀ ድር አማካኝነት ምዝገባው ይካሄዳል፡፡ ገፀ ድሩ ላይ በሶስት ዘርፎች ምርጫዎች አሉ፤ በመረጡት ዘርፍ እንዲሰለጥኑ ምደባ ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም ተመዝጋቢዎች የሚፈልጉትን ዘርፍ በመምረጥ እንዲመዘገቡ ተመቻችቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ቀኑን ሲያሳውቅ ምዝገባ የሚጀመር መሆኑንም አሰልጣኝ ስመኝ ጠቁመዋል፡፡
የኮሌጁ የሬጅስትራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደሚያስረዱት፤ ተቋሙ አዲስ ተመዝጋቢዎች ሲመጡ ብቻም ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ ስራም ይሰራል፡፡ የሚሰጠውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለማስተዋወቅና ዜጎች መጥተው እንዲሰለጥኑና የሙያ ክህሎታቸው የዳበረ እንዲሆን ከየትምህርት ቤቶች ጋር ስምምነት በመፈራረም በየጊዜው በቅንጅት ለመስራት እቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ ሌላ ኮሌጁ በኦን ላይን የስልጠና አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ይዟል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግም አሰልጣኞችን የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የማሰልጠኛ አስፈላጊ ግብዓት ከተመቻቸ በኋላ አገልግሎቱ እንደሚጀመርም ነው የገለፁት፡፡
“ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የሚሰለጥኑበትን ዘርፍ ሳያስቡበት በስሜት ይመርጡና ከጀመሩ በኋላ ወደ ሌላ ዘርፍ ቀይሩን የሚሉ ሰልጣኞች ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በጓደኞቻቸው ግፊት ይመርጣሉ፡፡ በመሆኑም ለመሰልጠን ለምዝገባ የሚመጡ ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚፈልጉ አካላት መጀመሪያ ስለሚሰለጥኑት የትምህርት ወይም የሙያ ዘርፍ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ምክንያቱም በቀጣይ ህይወታቸው ስራ የሚፈጥሩበት፣ የሙያ ባለቤት የሚሆኑበት በመሆኑ በጥንቃቄ ማሰብ፣ በፍላጎታቸው መሰረት መርጠው መመዝገብ፣ መሰልጠንና ሙያቸውን ማዳበር አለባቸው፡፡ ዘመን ተሻጋሪ በሆነው በዚህ ኮሌጅ በመምጣት መሰልጠንና የትልቅ ሙያ ባለቤት መሆን ይቻላል” ሲሉ አሰልጣኝ ስመኝ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ብቃት ባላቸው አሰልጣኞች እንዲሁም በስልጠና ግብዓትም ራሱን አደራጅቶ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረገው መሰናዶ የሚበረታታ ነው፡፡ በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች እየሰጠ ባለው ስልጠናም በርካታ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ያፈራና የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው የራሱን አሻራ ያሳረፈ ተቋም በመሆኑ በዚሁ ይቀጥል እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው