ወጣት እሸቱ አዲስ በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ ካገኙ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ ነው፡፡ አስር አባላት ያሉት “ወርቅነሽና ጓደኞቻቸው የእንጨት ስራ ማህበር”ን የመሰረተው በ2007 ዓ.ም ነበር፡፡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሲሆን በ9 ሺህ ብር ካፒታል ነበር ስራ የጀመሩት፡፡ ማህበሩ አልጋ፣ ቁም ሳጥን፣ ብፌ፣ ሶፋ፣ ጠረጴዛና ሌሎችንም የእንጨት ውጤቶች ያመርታል፡፡ ለ11 ዜጎችም የሥራ እድል ተፈጥሮል፡፡
ወጣት እሸቱ ስራውን ሲጀምሩ የሚጠቀሙት የምርቶች ዲዛይን እንደአሁኑ ገበያ ላይ ተፈላጊ እንዳልነበረ ያስታውሳል፡፡ “እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2016 ዓ.ም የሶፋ፣ የአልጋ፣ የጠረጴዛ፣ ወንበር ውጤቶች ዲዛይን የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ አድርጎልናል። የተደረገልንን ድጋፍ መጠቀም በመቻላችን የምናመርታቸው ምርቶች ከበፊቱ ተቀባይነት እያገኙ ነው፡፡ ባዛሮች ላይ በብዛት በተለይ የሶፋ ምርቶችን እናቀርባለን” ሲል የኮሌጁ ድጋፍ በስራቸው ላይ ለውጥ እንዳስገኘላቸው ይናገራል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉ በአጭር ጊዜ ብዙ ነገር ማምረት እንድንችልና ስራችንም ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሎናል፤ ይላል ወጣት እሸቱ። “በዋናነት ቀድሞ ምርቶችን በወርና በአስራ አምስት ቀን የምናደርሰውን አሁን በቴክኖሎጂው በተሰጠን ዲዛይን መሰረት በሳምንት እንዲሁም በአራትና በአምስት ቀናት አምርተን ለገበያ እንድናቀርብ አስችሎናል፤ እንድንለወጥም ረድቶናል። በዚህም ኮሌጁን አመሰግናለሁ፡፡ ለኢንተርፕራይዞች የሚያደርግልንን ድጋፍም ይቀጥልበት” ሲል ወጣት እሸቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለኢንተርፕራይዞች ምርታማነት ከሚሰጠው አጫጭር ስልጠና ባለፈ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት ማረጋገጫ የስራ ክፍል አስተባባሪ አቶ ኪሩቤል አከለ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፣ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት ማረጋገጫ የስራ ክፍል በኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ቴክኖሎጂ ሽግግር የስራ ክፍል ስር አንድ የስራ ዘርፍ በመሆን እየሰራ ይገኛል። ዋና ዓላማውም ለኢንተርፕይዞች የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረገው በቁሳዊ፣ ሰነዳዊ፣ የአሰራር ሥነ ዘዴ እና ኢንፎርሜሽን ሲሆን ውጤቱም ኢንተርፕራይዞች ጉልበት የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ጥራትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደቱ ከ2015 ዓ.ም በፊት የኮሌጁ አሰልጣኞች በተነሳሽነት ቴክኖሎጂዎችን በማጥናትና የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በመስራት የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ ይደረግ ነበር፡፡ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ አሰራሩን በመቀየር ኢንተርፕራይዞች ምን አይነት ዘመኑን የሚመጥን ማሽነሪ ይፈልጋሉ? የሚለውን መስሪያ ቦታቸው ድረስ ወርዶ ፍላጎታቸው ላይ መሰረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ቴክኖሎጂዎች ይሰሩና በሰነድ ሽግግር ይደረግላቸዋል፡፡
አቶ ኪሩቤል በማብራሪያቸው፤ ለአብነት የዳቦ ዱቄት ማቡኪያ ማሽን፣ ለሸክላ ስራ፣ ለዶሮ እርባታ፣ ለእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ ለእንጨት ስራና ሌሎችም የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች ተሰርተው የተሸጋገሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ሙሉ በሙሉ የእውቀት ሽግግር ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች ጋር በመሄድ የተዘጋጁ ቴክኖሎጂዎችን ሙሉ መረጃ በሰነድ ሽግግር ይደረጋል። ኢንተርፕራይዞችም የቴክኖሎጂውን ዲዛይን በሰነድ በመረከብና በማባዛት ወደ ስራ ለመግባት ውል ሲፈጽሙ ሽግግሩ እንደሚካሄድ፣ የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎችን በመምረጥም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በሚዘጋጁበት አውደ ርዕዮች፣ በቴክኒክና ሙያ ሳምንት በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፉን ከሰነድ ባለፈ ማሻሻያ በማድረግ አሰራሩን የመቀየር ክንውን መጀመሩንም አቶ ኪሩቤል ያነሳሉ። ይህም ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የቴክኖሎጂ ፍላጎት ጥናት በሚደረግበት ወቅት ኢንተርፕራይዞች የሚፈልጉትን መርጠው እንዲሰራላቸውና ገበያው ላይ ካለው በቅናሽ ዋጋ የጥሬ እቃና የጉልበት ወጪ ብቻ በማስላት ቴክኖሎጂው በጥራት በኮሌጁ አሰልጣኞች ተሰርቶ ገዝተው እንዲወስዱ የማድረግ እቅድ ተይዟል። ኢንተርፕራይዞች በፍላጎታቸው መሰረት የማምረቻ ቴክኖሎጂዎች ማለትም የአጃክስ ማምረቻ፣ የወተት ቅቤ ማውጫ፣ የእርጎ ማርጊያ እና የእህል መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ለመስራት ዲዛይኑ ተለይቷል፡፡ ግብዓት የመለየት፣ ማሽኖችን ለመስራት የሚያስፈልገው ዲዛይንና ቁሳቁስ ዝርዝር መግለጫ (ስፔሲፊኬሽን) የማውጣትና የዕቃ ግዢና ሌሎች አስፈላጊ ሂደቶች የሚከናወኑ ሲሆን ሲጠናቀቅ ማሽኖች ተሰርተው ኢንተርፕራይዞች እንደሚረከቡት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል አልፎ አልፎ በልብስ ስፌትና ሽመና ላይ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ላይ የአሰራር ሂደቱ ላይ የማሰልጠን ስራም እንደሚሰራ አስተባባሪው ይገልፃሉ፡፡ ለአብነት ከሹራብ ተረፈ ምርት አሻንጉሊት የመስራት ክህሎት እንዲኖራቸው የተደረጉ አሉ፡፡ ጀማሪዎች ፈጠራቸውን የሚያዳብሩበት (የኢንኩቤሽን ማዕከል) በማደራጀት ተመራቂ ተማሪዎች፣ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችና ከስደት ተመላሾች የንግድ፣ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች መሰረታዊ የሆነ የኢንተርፕረነርሺፕ፣ የቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀት ላይ የማሰልጠን ስራም ተሰርቷል፡፡ በ2016 ዓ.ም 35 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ሰልጥነው ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
በቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት ማረጋገጫ የስራ ክፍል በአብዛኛው ከጉለሌ እና ሌሎች ክፍለ ከተሞች ለሚመጡ ኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ድረስም የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን ለ86 ኢንተርፕራይዞች ሽግግር በማድረግ መደገፍ መቻሉንና ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነታቸው መጨመሩ አንድ ውጤት መሆኑን አቶ ኪሩቤል ይገልፃሉ፡፡
በቀጣይም ክፍሉ ለኢንተርፕራይዞች እያደረገ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ በማስቀጠል 5 የማምረቻ፣ 8 የምርትና 1 የሀገር በቀል ቴክኖሎጂ የመስራት እቅድ ተይዟል፡፡ ኢንተርፕራይዞች በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በመሰማራት የራሳቸውን ገቢ እንዲያበለፅጉ የተለያዩ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የመስራትና የመሸጥ እንዲሁም ክፍተቶቻቸውን የመለየትና መፍትሄ የመስጠት ስራ እንደሚቀጥልም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንተርፕራይዞች ገበያው የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ ማድረጉ ስራቸው ውጤታማና ምርታማ እንዲሆን አበርክቶው በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ በዚሁ ቢቀጥል እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው