የኮሌጁ ጓሮ በረከት

ወይዘሮ ወርቂቱ ገብሬ በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በፅዳትና ተላላኪነት ሙያ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ኮሌጁ ዝቅተኛ የወር ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ ሰራተኞቹ ባመቻቸው እድልም በግቢው ባለ ቦታ በከተማ ግብርና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡

“ኮሌጁ መሬት ሰጥቶ ‘አምርታችሁ ብሉ፣ ገቢ አግኙ’ ማለቱ መልካም ስራ ነው፡፡ በተሰጠኝ ቦታ ላይ እንደ ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ ያሉ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት የምግብ ፍጆታዬን ከመሸፈን ባለፈ ለተቋሙ ሰራተኛና ለአካባቢው ማህበረሰብ በመሸጥ ገቢ እያገኘሁ ነው፡፡ ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች ትልቅ ድጎማ እና እገዛ ነው የተደረገልን፡፡” ሲሉ ይህን እድል ላመቻቹት የኮሌጁ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

በኮሌጁ የጥበቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ቢራራም የዚሁ እድል ተጠቃሚ ናቸው። “ግቢው ሰፊ በመሆኑ በከተማ ግብርና መስራት የሚፈልግ ሰርቶ መጠቀም ይችላል” ብለው የኮሌጁ አመራሮች በሰጧቸው እድል አትክልት በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

በኮሌጁ የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ሰለሞን ቢራራ

“አትክልቶችን ከውጪ አልገዛም፡፡ እንዳመርትበት በተሰጠኝ ቦታ ቆስጣ፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቃሪያ፣ ድንች በማምረት የምግብ ፍጆታዬን እሸፍናለሁ፡፡ በቆሎም አምርቻለሁ። ከዚህ አልፎ ለሰራተኛውና ለአካባቢው ማህበረሰብ በመሸጥ ገቢ እያገኘሁ ነው፡፡ ይህን ትልቅ እድል ለሰጡን የተቋሙ አመራሮች በጣም አመሰግናለሁ፡፡” ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ አንዱ በሆነው የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት ስራዎች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም የቤት ውስጥ ፍጆታ ከመሸፈን አልፈው ለገበያ በማቅረብ ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው፡፡ 

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከሚሰጠው የማሰልጠን ተግባር ጎን ለጎን በተቋሙ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞችን ለመደገፍ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በፍላጎታቸው በግቢው ባለው መሬት በከተማ ግብርና እንዲሰሩና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን በኮሌጁ የህንፃ አስተዳደር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አላዬ ጉችዬ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ ገልፀዋል፡፡

ኮሌጁ ለዚህ ተግባር መነሻ የሆነውን ምክንያትን አቶ አላዬ ሲያብራሩ፤ እንደ ሀገርና እንደ ከተማ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና እንዲሰራ በወረደው አቅጣጫ መሰረት በኮሌጁ የሚገኙ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች በዚህ ዘርፍ ቢሰሩ ገቢያቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ በሚል ተነሳሽነት የተጀመረ ነው፡፡ የከተማ ግብርና ስራውን በተቋም ደረጃ ለመስራት ከወንድይራድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሞክሮ በመውሰድ ከተቋሙ አመራሮች ጋር በመነጋገር ወደ ተግባራዊ ስራ ተገብቷል፡፡፡ የወር ደመወዛቸው ከ1 ሺህ 600 እስከ 3 ሺህ ብር የሆኑ ሰራተኞች በኮሌጁ መልማት የሚችል 2 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እያለሙ ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ኃላፊው እንደሚገልፁት፤ ሰራተኞቹ የሚፈልጉትን ምርት እንዲያመርቱ ቦታ ከመስጠት ባሻገር ለስራቸው አስፈላጊ የሆኑ የመኮትኮቻ መሳሪያ፣ የውሃ አቅርቦትና የተለያዩ ግብአቶች ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

ኮሌጁ ከዝቅተኛ ተከፋይ ሰራተኞች ባለፈ በግቢ ያለውን መሬት መንጥሮ መስራት የሚችል በማንኛውም ደረጃ ተከፋይ የሆኑና ፍላጎት ያላቸው የተቋሙ ሰራተኞች በከተማ ግብርና በመስራት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት አሰራር ለማስፋት እቅድ ይዟል። ከዚህ አልፎ እየተሠራ ያለውን ስራ ለሌሎች በተሞክሮነት የማስተላለፍ ስራም ተሰርቷል። በግብርና ዘርፍ የተሰማሩና ከክፍለ ከተሞች የመጡ ሰዎች ተሞክሮ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ስራ የተሰማሩት ዝቅተኛ ተከፋይ የኮሌጁ ሰራተኞች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለአትክልት ከሚያወጡት ወጪ ድነው በራሳቸው ንፁህ አትክልት አምርተው ይመገባሉ፡፡ የተረፋቸውን ለኮሌጁ ማህበረሰብ እንዲሁም ለአካባቢው ህብረተሰብ የሚሸጡበትና በደመወዛቸው ላይ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ትልቅ ውጤት ያመጣ መሆኑን አቶ አላዬ ተናግረዋል፡፡

ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ወንድ 45 ሴት 46 ሰራተኞች በድምሩ 91 ዝቅተኛ ደመወዝ የሚያገኙ ሰራተኞች በከተማ ግብርና በግቢው በመስራት ገቢ እያገኙ መሆኑን የኮሌጁ መረጃ ያመለክታል፡፡

በቀጣይ ሰራተኞቹ ከከተማ ግብርና ባለፈ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ እና ሌሎች የሌማት ትሩፋት ዘርፎች ሰርተው እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ሌላ ሰራተኛው የተጨማሪ ሙያ ባለቤት መሆን ስላለበት ፍላጎት ያላቸው ሰራተኞች በከተማ ግብርና፣ ልብስ ስፌት እንዲሁም በሌሎች ኮሌጁ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች ሰልጥነውና ተደራጅተው በግቢው ባለው ሀብት መጠቀም የሚችሉበት እድልም የተመቻቸ በመሆኑ ፍላጎት ያለው ሰራተኛ መጠቀም እንደሚችል አቶ አላዬ አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከሰራተኞቹ ተጠቃሚነት ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን በሴፍትኔት ተደራጅተው የሚደገፉ ሴቶችና ወጣቶች ሰርተው ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የበኩሉን ማህበራዊ ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑንም አቶ አላዬ ያነሳሉ፡፡ ወደ አንድ ሄክታር የሚሆን ቦታ በነፃ በመስጠት በከተማ ግብርና እየሠሩ ገቢ እያገኙ ነው፡፡ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 እና 3 የሚገኙ ወንድ 16 ሴት 115 የሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ኮሌጁ በሰጣቸው ቦታ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ከሚሰጠው የስልጠና አገልግሎት ባለፈ ሰራተኞቹን ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሁም በሴፍቲኔት የታቀፉ ዜጎችን በመደገፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ አላዬ ያስረዱት፡፡

እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከማሰልጠን ተግባሩ ጎን ለጎን ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞቹ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያደረገ ያለው ድጋፍ እጅግ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው፡፡ ለሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ ስለሚሆን ተግባሩ በዚሁ ይቀጥል እንላለን፡፡

ሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review