የኮሌጆቹ መሰናዶ ሲቃኝ

You are currently viewing የኮሌጆቹ መሰናዶ ሲቃኝ

• የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆቹ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው ለማሰልጠን አቅደዋል

ወርሃ መስከረም፤ በኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር መሠረት የዓመቱ መጀመሪያ ነው፡፡  ከሌሎች  ወራት ቀድሞ ከመቀመጡ  በተጨማሪ የተለየ ገፅታን እንዲላበስ በተፈጥሯዊና ሠው ሰራሽ ሁነቶች የመታጀብ ዕድልን ተችሮታል፡፡ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች በአዲስ ንቃት፣ በአዲስ አቅም፣ በደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ተውበውና እንደ አደይ አበባ ደምቀው የሚታዩበት ተናፋቂ ጊዜም ነው፤ ወርሃ መስከረም፡፡

ለትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው ሙሽሮቻቸው ናቸው፡፡ ያለ ተማሪዎች የትምህርት ተቋም አይታሰቡም፡፡ ለዚህም ነው በክረምቱ ወራት በራቸውን የዘጉት የትምህርት ተቋማት፣ ከተዘጋው በር ጀርባ በቅጥረ ግቢያቸው ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የሚቆዩት፡፡ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር ተማሪዎቻቸውን ባለፈው የትምህርት ዘመን በነበራቸው መልክና ገፅታ አይቀበሏቸውም። ከአምናው ተሽሎ ለመገኘት፣ ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹና ውጤታማ ለመሆን ያላቸውን አቅም  ይጠቀማሉ። መማሪያ ክፍሎች ይፀዳሉ። ቅጥረ ግቢው ይዋባል፡፡ የትምህርት ግብዓቶች ይሰናዳሉ፡፡ ልክ አዲስ ሙሽራ እንደሚቀበል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ያሰናዳሉ፡፡

የትምህርት ተቋማት ለወርሃ መስከረም የሚሰጡትን የተለየ ገፅታ እዚህ ላይ ገታ አድርገን በጽሁፋችን ለመቃኘት ወዳሰብነው ጉዳይ እናቅና፡፡ ጉዳያችን ከተነሳንበት ሃሳብ የራቀ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት መካከል የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በ2017 የትምህርት ዘመን ሰልጣኞቻቸውን በምን አግባብ ተቀብለው ለማሰልጠን እንደተዘጋጁ የሚቃኝ ነው፡፡ ለዚህም የዝግጅት ክፍላችን በመረጃ ምንጭነት የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች አነጋግሯል፡፡ 

አቶ ኢንድሪስ ሙሃመድ ይባላሉ፤ በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን ናቸው፡፡ እሳቸው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን እያደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ “በ2017 የትምህርት ዘመን አዳዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ከዝግጅታችን መካከል አንዱ በኮሌጁ አቅራቢያ የሚገኙ አራት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (ደጃዝማች ባልቻ፣ ዕውቀት ለሕብረት፣ ዕውቀት ለፍሬ እና ድላችን ሁለተኛ ደረጃ) ጋር በመገናኘት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አከናውነናል። የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው ስለ ቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ስልጠና ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ግንዛቤው ለተማሪዎች፣ ለተማሪ ወላጆች፣ ለመምህራንና ለትምህርት አመራሮች ተሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም በኮሌጁ በአካል በመገኘት እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ ይህም ከዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ያላቸውን ፀጋ በአግባቡ እንዲረዱ ያግዛል፡፡ ለኮሌጁ የቅበላ አቅም ከፍ ማለትም አስተዋፅኦ ያበረክታል” ብለዋል፡፡

“በትምህርት ዘመኑ ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሊገቡ የሚችሉ ተማሪዎችን ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በ2017 የትምህርት ዘመን የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 1 ሺህ 529 አዳዲስ ሰልጣኞችን እንዲቀበል ዕቅድ ወርዶለታል” ያሉት በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን፤ ኮሌጁ ከዕቅዱ በላይ ሰልጣኞች ቢመጡ ተቀብሎ ለማሰልጠን የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ መሰረት በ2017 የትምህርት ዘመን የመደበኛ ሰልጣኞችን ጨምሮ 3 ሺህ 240 ሰልጣኞችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በስራቸው 28 ሙያዎችን ባካተቱ 11 የሥልጠና ዘርፎች ሰልጣኞችን በመቀበል ከደረጃ አንድ እስከ አራት ድረስ ያሰለጥናል። ሥልጠናዎቹ በዋናነት የገበያውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። በኮሌጁ ካሉት የስልጠና ዘርፎች መካከልም የብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች (ሌዘር)፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት (ጋርመንት) እና አውቶሜካኒክ ይጠቀሳሉ። ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ በክረምቱ ወራት ውስጥ ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ራሱን በሠው ኃይል፣ በግብዓት፣ በቤተ ሙከራ (ወርክሾፕ) የማጠናከር እና የማደራጀት ሥራ ሠርቷል፡፡ የስልጠና ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ማሽኖች የመሳሰሉትን ለሥልጠና ዝግጁ አድርጎል። አዲስ ሰልጣኞች በኮሌጁ የበለጠ እንዲሳቡ ቅጥረ ግቢውን አረንጓዴ፣ ሳቢና ምቹ ማድረግም ተችሏል፡፡  

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2017 የትምህርት ዘመን አዳዲስ እና ነባር ሰልጣኞችን ተቀብሎ በተሻለ ሁኔታ ለማሰልጠን ተገቢውን ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ የኮሌጁ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ አንተነህ ሙሉ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት ከሆነ፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ቁጥራቸው 2 ሺህ 40 የሚሆኑ አዳዲስ ሰልጣኞችን በመቀበል በመደበኛው የስልጠና መርሃ ግብር (በቀን፣ በማታ እና በቅዳሜና እሁድ) ለማሰልጠን አቅዷል፡፡ ይህ ዕቅድ ከ3 ሺህ 500  በላይ ከሆኑት ነባር ሰልጣኞች ጋር ተደምሮ የኮሌጁ የ2017 የትምህርት ዘመን የሰልጣኝ ቁጥር ከ5 ሺህ 500 በላይ ያደርሰዋል። ለትምህርት ዘመኑ አስፈላጊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በዋናነት የስልጠና ቤተ ሙከራዎችን (ወርክሾፖችን) የማደራጀት፣ የስልጠና ግብዓት ግዢ የመፈፀምና የማስገባት፣ የአሠልጣኞችን አቅም የመገንባት ሥራ ተከናውኗል፡፡

የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማሰልጠኛ ወርክሾፕ ከፊል ገፅታ

በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ አንተነህ ሙሉ አክለው እንዳስረዱት፤ ወደ ኮሌጁ አዳዲስ ሰልጣኞችን በዋናነት የሚልኩት የደጃዝማች ባልቻ እና የሕዳሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ አቅራቢያ የሚገኙ በመሆናቸው ነው ተማሪዎቻቸው በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ የቅበላ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው። የቅበላው ሂደት የተሳካ እንዲሆን ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንና መምህራን ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው፡፡ ለተማሪና ለተማሪ ወላጆች ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ስለ ኮሌጁ አጠቃላይ ሁኔታ ለማስገንዘብ የሚያስችል መድረክ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ተከታታይነት ያለው መረጃ በኮሌጁ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ሌሎች የሚዲያ አማራጮችንም ለመጠቀም እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአስር የስልጠና ዘርፎች (Departments)፣ በሃያ ሁለት የሙያ ዓይነቶች (Occupations) ከደረጃ ሦስት እስከ ደረጃ አምስት ድረስ ነባርና አዳዲስ ሠልጣኞችን ያሰለጥናል። ኮሌጁ ከሚሰጣቸው የስልጠና ዘርፎች መካከል፡- የአውቶሞቲቭ፣ ኤሌክትሪክሲቲ፣ ባዮሜዲካል፣ ማኑፋክቸሪኒንግ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)፣ ይጠቀሳሉ።  ስልጠናዎቹም በዋናነት የገበያውን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ በከተማ አስተዳደር ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የሚሰጡ በርካታ የመንግስት እና የግል ተቋማት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስድስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ ስምንት ኮሌጆች እንዲሁም በፖሊ ቴክኒክ እና በቴክኒክ ኮሌጆች የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞችንና አመራሮችን አቅም ለመገንባት የተቋቋመ አንድ የልህቀት ማዕከል በመንግስት የሚተዳደሩ ናቸው። ቁጥራቸው 114 የሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች እና ተቋማት ደግሞ በግሉ ዘርፍ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ለ2017 የትምህርት ዘመን እያደረጉ ስላለው ዝግጅት በሥራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሱፐርቫይዘር አቶ ታደለ አየነውን አነጋግረናቸዋል። እሳቸው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ በከተማ አስተዳዳር ደረጃ ያሉ የመንግስት የቴክኒክና  ሙያ  ማሰልጠኛ  ኮሌጆች በ2017 የትምህርት ዘመን አዳዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የትምህርት ዘመን እንደ ከተማ አስተዳደር 30 ሺህ 390 አዳዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ታቅዷል፡፡ የዕቅዱ መነሻም በ2016 የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደርደረጃ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ቁጥር ከትምህርት ቢሮ በመውሰድ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በከተማ አስተዳደሩ ያሉ የመንግስት ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በ2017 የትምህርት ዘመን እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ አዳዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም አላቸው፡፡ ከዚህም በላይ የሰልጣኝ ቁጥር ቢመጣ የማስተናገድ አቅሙ አለ፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ያለው ልምድ የሚያሳየው ወደ ኮሌጆች የሚመጣው የሰልጣኝ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስክ ያለው የግንዛቤ ችግር ነው፡፡

አቶ ታደለ እንደገለፁት፤ አዳዲስ ሰልጣኞች ወደ ማሰልጠኛ ኮሌጆቹ እና ተቋማቱ ገብተው ጥራት ያለው ሥልጠና እንዲያገኙ፣ በሙያና በክህሎት እንዲበቁ አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ የክረምቱን ወራት ጨምሮ በትኩረት ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በዚህም ለስልጠና የሚሆኑ ማንዋሎች እና ቁሳቁሶች በአግባቡ ተዘጋጅተዋል፡፡ መሻሻል የሚገባቸው ተሻሽለዋል። በመንግስት የሚተዳደሩት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሰልጣኞችን በዋናነት የሚቀበሉት ከመንግስት ትምህርት ቤቶች በመሆኑ፤ የሥራ ሂደቱ በውጤታማነት እንዲከናወን በየደረጃው በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ በመፈራረም ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በዚሁ መሰረት የከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ እና ትምህርት ቢሮ በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በከተማዋ ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ዝርዝር መረጃ የሥራና ክህሎት ቢሮ ከትምህርት ቢሮ ወስዷል፡፡

በተመሳሳይ፤ በከተማዋ ያሉ  አስራ አራት የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች አዳዲስ ሰልጣኞችን እንዲቀበሉ ከተመደቡላቸው በአቅራቢያቸው ካሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በስምምነታቸው መሰረት ሲሠሩ ቆይተዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ። ይህም የየትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ አመራሮች እና የተማሪ ወላጆች ወደ ኮሌጆቹ በመሄድ እንዲጎበኙ ዕድል ይፈጥራል። የኮሌጆቹን የማሰልጠን አቅም እና ዝግጁነት በሚመለከቱት እና በሚሰጣቸው ገለጻ፣ ከቅጥረ ግቢ ጀምሮ የማሰልጠኛ ክፍሎቹን፣ የቤተ ሙከራዎቹን (ዎርክሾፖች)፣ የግብዓት እና የአደረጃጀት ነባራዊ ሁኔታ፣ የሠው ኃይሉን ብቃትና ስብጥር በመታዘብ ስለተቋማቱ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ እየተደረገ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የኮሌጆቹ ቅጥረ ግቢ ውብና ፅዱ ሆኗል። በከተማዋ ተተግብሮ ውጤታማ የሆነውን የኮሪደር ልማት ዓይነት ሥራ ኮሌጆቹ በቅጥረ ግቢያቸው ተግብረውታል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ያሏቸውን የስልጠና ቤተ ሙከራዎች (ወርክ ሾፖች) ለአዲሱ የትምህርት ዘመን በተሻለ ሁኔታ ዝግጁ እየተደረጉ መሆናቸውን ያነሱት በሥራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሱፐርቫይዘር አቶ ታደለ፤ የተበላሹ እና ጥገና የሚያስፈልጋቸው ማሽኖች በየኮሌጆቹ በተዋቀረው የጥገና ቡድን አማካኝነት እየተጠገኑና ለአገልግሎት በመሰናዳት ላይ ናቸው፡፡ ይህም ኮሌጆቹ ያላቸውን የውስጥ አቅም በመጠቀም ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ አብዛኞቹ ጥገናዎች በውስጥ አቅም መከናወን መቻላቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ የማሽኖቹ ብልሽት ከውስጥ አቅም በላይ ከሆነ  በውጭ አቅም ይጠገናሉም ብለዋል፡፡ 

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና 70 ከመቶው የተግባር፣ 30 በመቶው ደግሞ የንድፈ ሃሳብ ይዘት ያለው ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ሰልጣኞች ብቁ ሆነው እንዲወጡ ከፍተኛ መጠን ያለው የማሰልጠኛ ግብዓት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ኮሌጆቹ ለስልጠና የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት ጨረታ የማውጣትና ግዢ የመፈፀም ሂደትን ቀደም ብለው የጀመሩ መሆናቸውን ዘርፉን  በበላይነት በከተማ ደረጃ የሚከታተለው እና ድጋፍ የሚያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ሥራና ክህሎት ቢሮ መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የግዢ ሂደታቸውን አጠናቅቀው ግብዓቶችን ወደ ተቋማቸው ያስገቡ ኮሌጆች ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኞቹ በሂደት ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በግዢ ሂደቱ ላይ የሚታየው የተለመደ መጓተት አሁን ሙሉ ለሙሉ ያልተቀረፈ መሆኑ በምክንያትነት ተነስቷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙት የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ሰልጣኞቻቸውን የመመዝገቡ ሂደት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ቅርበትን መሰረት ያደረገው ትምህርት ቤቶችን የመደልደል አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ አሳውቋል። በዚሁ መሰረት፤ ሁሉም የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ የታገዘ የኦንላይን አገልግሎትን የሚተገብሩ ይሆናል፡፡ ይህ ተግባር በ2016 የትምህርት ዘመን የተጀመረ ሲሆን፤ በወቅቱ የታዩ ጉድለቶችን በማስተካከል በዘንድሮው የምዝገባ ሂደት ላይ ውጤታማ እንዲሆን በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በሙከራም ውጤታማነቱ ተረጋግጧል፡፡

አዳዲስ ሰልጣኞችን ወደ ማሰልጠኛ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የመመደቡ ተግባር የሚከናወነው በዋነኛነት ቅርበትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በከተማዋ ቁጥራቸው ሰማኒያ የሚደርሱ የመንግስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በከተማዋ ካሉ አስራ አራት የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መካከል በአንፃራዊነት ቅርብ ወደሆኑባቸው ሄደው የሚመዘገቡ ይሆናል፡፡ ይህ ሰልጣኞች በአቅራቢያቸው ሆነው ሥልጠናቸውን እንዲወስዱ ያግዛል፡፡ የኮሌጆቹን የቅበላ መጠን እና የሠልጣኝ ስብጥር ሚዛን ያስጠብቃል፡፡ አሠራሩ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ሙሉ በሙሉ የሚተገበር ሲሆን፤ የተለየ እና አሳማኝ ምክንያት ካጋጠመ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎች በገበያው ላይ በጣም ተፈላጊ ናቸው፡፡ በግላቸውም ሆነ በማህበር ተደራጅተው በመሥራት ለውጤት የሚበቁበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ከራሳቸው አልፎ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ አማራጭ ለመሆን ችለዋል፡፡ ለማህበረሰቡ እና ለአገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታንም እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ሰልጣኞች ራሳቸውን በሂደት በስልጠና የሚያበቁበት እና ደረጃቸውን ከፍ የሚያደርጉበት አዲስ አሠራር መተግበሩ ዘርፉን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ሙያቸውን በትምህርትና በስልጠና በማሳደግ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርስቲዎች) ተምረው እንደሚወጡ ተማሪዎች የሁለተኛ፣ የሦስተኛ ድግሪያቸውን እና ከዚያም በላይ ያለውን ደረጃ ማሳካት የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ስለሆነም በሙያ፣ በክህሎት፣ በዕውቀት እና በብቃት አሰልጥነው ራስን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን እና አገርን ለመጥቀም ወደሚያስችሉት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በመግባት ከጥቅማቸው ተቋዳሽ መሆን የአገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች የሚጠበቅ ነው እንላለን፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review