AMN- ህዳር 11/2017 ዓ.ም
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለ ጦር ባደረገው ተከታታይ አሰሳ በፅንፈኛዉ ቡድን ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን የኮማንዶ ሻለቃ አዛዥ ሻለቃ ወርቁ አደሬ ገልፀዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛና ግሼ ራቤል ወረዳዎች በተደረጉ ዘመቻዎች ከመደምሰስ የተረፉ የፅንፈኛዉ ቡድን አባላትን ጨምሮ ቡድኑ ሲጠቀምባቸዉ የነበሩ ተሽከርካሪዎች፥የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እንደ ሻለቃ አዛዡ ገለፃ በዋናነት በሠራዊቱ የተማረኩት ተሽከርካሪዎች ከአሁን ቀደም የወረዳዉ ንብረቶች የሆኑና የማህበረሰብ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሲሆን፤ ቡድኑ ተሽከርካሪዎቹን በመዝረፍ ለራሱ እኩይ አላማ ሲጠቀምባቸዉ የቆየ ሲሆን አሁን ላይ ግን ንብረቶቹ በክፍለጦሩ አማካኝነት ለወረዳዉ ገቢ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

በተመሳሳይ የአየር ወለድ ሬጅመንት በሰሜን ሸዋ ዞን በመርሐ ቤቴ ወረዳ የተበታተነውን የፅንፈኛ ሀይል እያፀዳ መሆኑን የሬጅመንት ዋና አዛዥ ቫለቃ የሺዋስ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ሬጅመንቱ በተከታታይ አሰሳና ስምሪት በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራቱ ተገልጻል፡፡

በተደረጉ ስምሪቶችም የፅንፈኛ ሀይሉን አባላት ከነትጥቃቸው መማረክ እና ይህንን ፀረ-ህዝብ የሆነ ሀይል የመመንጠሩን ስራ ሬጅመንቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አዛዡ መናገራቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ የትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።