AMN-መስከረም 20/2017 ዓ.ም
በሀረር ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በገጠር ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በሀረር ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶችን በወረዳ ደረጃ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከወረዳ አመራሮች ጋር መክረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በምክክሩ ላይ፣ በሀረር ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ ስራውን በወረዳዎች ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ለመንገድ ስራ 1 ቢሊየን የሚደርስ ብር መመደቡን በማመላከት በከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶች ማስፋፊያ እንዲሁም በገጠር ወረዳዎች አዳዲስ የኮሪደር ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተለይ በገጠር ወረዳዎች ሰፋፊ፤ ፅዱ እና ምቹ የዕግረኛ እና መኪና መንገዶች እንዲኖሩ በማስቻል የሚስተዋለውን የመንገድ ላይ ንግድ እና ፅዳት ችግር ስርዓት ለማስያዝ የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኮሪደር ልማቱ በወረዳዎቹ በቀጣይ በሚከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የገበያ ቦታዎችን ፅዳት እና ውበት መጠበቅ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ለሚያመነጨው ቁሻሻ ተገቢውን ክፍያ እንዲፈፅም በማድረግ ገበያውን ስርዓት ማስያዝ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል አመራሩ ህገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በከተማ እና ገጠር ወረዳዎች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችን የክልሉ ካቢኔ አባላት በወረዳዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ መስጠታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።