የኮሪደር ልማት ሀገራዊ የክትመት ስርዓትን በተጨባጭ የቀየረ እሳቤ ነው፡-ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ

You are currently viewing የኮሪደር ልማት ሀገራዊ የክትመት ስርዓትን በተጨባጭ የቀየረ እሳቤ ነው፡-ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ

AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም

የኮሪደር ልማት የከተማ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ሀገራዊ የክትመት ስርዓትን በመሰረታዊነት እየቀየረ የሚገኝ እሳቤ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በከተማና በገጠር የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ ነው።

ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ የሌማት ትሩፋት፣ የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ እንዲሁም በከተሞች የኮሪደር ልማት ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊና የፓርቲው አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል።

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ ፓርቲው በውይይቱ የከተሞች የኮሪደር ልማት በተያዘለት እቅድ መሰረት በውጤታማነት እየተተገበረ መሆኑን ተመልክቷል ብለዋል።

አቶ ሙስጠፌ 57 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በከተማ እንደሚኖር መረጃዎችን በዋቢነት ጠቅሰው፥ መንግሥት እየተገበረ ያለው የኮሪደር ልማትም የከተሞችን ዕድገት ከግምት ያስገባ ነው ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት እስከ 70 በመቶ የዓለም ህዝብ ከተሜ ይሆናል የሚለውን ትንበያ ታሳቢ ያደረገና ዘመናዊ የክትመት ስርዓትን የመገንባት ግብ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አድማሱን አስፍቶ በክልል ከተሞች ገቢራዊ እየተደረገ ያለውም የዚህ ሩቅ አሳቢነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ኤሌክትሪክ፣ ድልድይ፣ የአስፋልት መንገድና ሌሎች ክትመትን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶችን መገንባት መሆኑን የገለጹት አቶ ሙስጠፌ፤ ይህም የእሳቤውን ስትራቴጂካዊነት በግልፅ የሚያመላክት መሆኑን አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ምቹ የመኖሪያና መዝናኛ ሥፍራዎችን በመገንባት በመዲናዋ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም በክልል ከተሞች ገቢራዊ መደረጉ የኢትዮጵያን የክትመት እንቅስቃሴ እያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዳዲስ እሳቤዎችና ፈጠራዎች መልካም ነገር ይዘው ሲመጡ ውጤታቸው በረዥም ጊዜ ሊታይ የሚችል ቢሆንም የኮሪደር ልማት ስኬቶቻችን ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመፈጸም አቅማችንን ያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ከተሞች መካከል ጅግጅጋ ቀዳሚዋ መሆኗን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ የኮሪደር ልማቱን ጥቅም በውል ተገንዝቦ በባለቤትነት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተሰሩ ፕሮጀክቶች ውብ እና ጎብኚዎችን የሚስቡ በመሆናቸው የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እያሳደገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ከተሞችን ዘመናዊ ለሰው ልጅ ምቹና ተስማሚ በማድረግ ጎብኚዎችን ለመሳብ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review