AMN-የካቲት 6/2017 ዓ.ም
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት ከ ጆርካ ኢቨንት ጋር በመተባበር የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ እና የስራ ባህል እንዲቀየር በማድረግ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ኮንትራክተሮች እና ባለሙያዎች የምስጋና እና የእራት ግብዣ መርሃግብር አካሄዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀምበር፣ የኮሪደር ልማት ስራ ጊዜያዊ እና አብረቅራቂ ሳይሆን ዘላቂ እና በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ስራ ነው ብለዋል።
ከአራት ኪሎ – ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል ኮሪደር ያለው የኮሪደር ልማት ስራ በፍጥነት እና በጥራት እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ልማቱ ዘመናዊ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገድ ያካተተ ለቀጣይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ስራ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ በጀመራቸው ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና አፈጉባኤ አቶ መኩሪያ ጉሩሙ ተናግረዋል ።
የምስጋና እና በእራት ግብዣ መርሃግብር ላይ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ግዛቸው አይካ ፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይከበር ስማቸው እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በዳንኤል መላኩ