የኮንፈረንስ ቱሪዝም እርካብ

You are currently viewing የኮንፈረንስ ቱሪዝም እርካብ

በዓለም ላይ በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚንቀሳቀሱባቸው በርካታ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ጉባኤዎች ይካሄዳሉ። ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተርስ የተሰኘ ገፀ ድር ያወጣው መረጃ እንደሚያትተው፣ ከእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ‘ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተርስ ኮንሰንትሬሽን ኤንድ ኢኮኖሚካል ቤኔፊት’ በሚል ርዕስ ለንባብ በበቃው በዚህ ጽሑፍ ዓለም በየዓመቱ ከምታሰናዳቸው ከእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ አፍሪካ የምታዘጋጀው ከ3 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህም በቂ የስብሰባ ማካሄጃ አዳራሽና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን ባለማሟላቷ እንደሆነ ተመላክቷል።

ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ከሚያስፈልጉ መሠረተ ልማች መካከል የኤግዚቢሽን እና ኮንቬንሽን ማዕከላት ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የሚያትተው መረጃው፣ በዓለም 1 ሺህ 500 የኮንቬንሽን ማዕከላት ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ ውስን ነው፡፡ በእርግጥ  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውስን መነሳሳቶች እንዳሉ አስፍሯል፡፡ በተለይ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ እና ርዋንዳን የመሳሰሉ ሀገራት በመልካም ደረጃ ላይ ይገኛሉ ይላል፡፡

አሁን ኢትዮጵያም ዘርፉን ተቀላቅላለች፡፡ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ገንብታ ወደ አገልግሎት አስገብታለች። ማዕከሉ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትልልቅ አዳራሾች፣ 10 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 1 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አልጋዎችን የያዙ 2 ሆቴሎች፣ 2 ሺህ መኪናዎችን የሚይዝ ፓርኪንግ፣ 50 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የኤግዚቢሽን ስፍራ እና ሁለት አንፊ ቴአትር፣ ሬስቶራንቶች፣ የንግድ ሱቆች፣ ባንኮች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የያዘ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገፅ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዓለም አቀፍ ኹነቶችን በመሳብ ሀገራችንን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት አንድ ተጨማሪ ዐቅም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱም፤ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና ዓለም አቀፍ ኹነቶችን በመሳብ ሀገራችንን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ አክለዋ፡፡

ለመሆኑ የዚህ ማዕከል መገንባት ለአዲስ አበባ እንዲሁም ለሀገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዴት ይታያል? ያልናቸው የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኝ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን፣ ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ማዕከላትን በማዘጋጀቷ በበርካታ ምክንያቶች ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሻለ ስትራቴጂካዊ ዕድሎች ያሏት በመሆኑ ተጠቃሚነቷን ያጎሉታል ብለው ጉዳዩን ወደ ማብራራት ዘልቀዋል፡፡

አቶ ኪሩቤል በሰጡን ማብራሪያ፣ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷን ከምታረጋግጥባቸው የሁነት ማሰናጃ ቦታዎች መካከል አንዱ ከመሆን አልፎ ቀላል ግምት የማይሰጠው የኢኮኖሚ ስህበት ማዕከል ይሆናታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አንፃር የማዕከሉ አዋጭነት አስተማማኝ እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ ኪሩቤል፣ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ፣ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ፣ የበርካታ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መናገሻ፣ ምቹ የአየር ፀባይ ያላት፣ በህዝብ ብዛትም በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ ማዕከሉ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንዲያመጣ ያስችሉታል የሚል ነጥብ አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ልማትና አስተዳደር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር) በበኩላው፣ አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም መዳረሻነት ተመራጭ የሚያደርጓትን ልማቶች እያከናወነች መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በኮንፍረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ባላት አቅም ልክ ለመጠቀም ዕድሉን እንደሚፈጥርላት ገልፀዋል፡፡

የመዲናዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይገባል የሚሉት ሽፈራው (ዶ/ር)፣ ማዕከሉን እንደ ገቢ ማስገኛ ብቻ እንደማይመለከቱትና የሀገርን ገጽታ በመቀየርና እምቅ የቱሪዝም አቅምን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ እገዛ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኮንፍረንሶች ሲካሄዱ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥቅሞችን ይዘው እንደሚመጡ ጠቅሰው፣ ለአውሮፕላንና ለሆቴል የሚያወጡትን ወጪ ጨምሮ ለምግብ፣ ለመዝናኛ፣ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ ጌጣጌጦችና አልባሳትን ለመሸመት የሚከፍሉት ገንዘብ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ በቱሪዝም መሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሽፈራው (ዶ/ር)፣ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከሚያስፈልጉ ሀብቶች መካከል ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከላትና የጉዞ ወኪሎች ተጠቃሽ ናቸው ሲሉ አክለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ  ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን አስመልክቶ በቅርቡ እንደገፁት በኢትዮጵያ ትልቁ የኮንፍራንስ ማዕከል መሆኑንና ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሁነቶችን በብቃት የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኝ የሆኑት አቶ ኪሩቤልም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ። አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ተቋማት መናገሻነቷ እንደምትታወቅ አውስተው፣ ከጄኔቫ እና ኒዮርክ ቀጥሎ ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል እንደመሆኗ ይህን ማዕከል ማዘጋጀቷ ቀላል ግምት የማይሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያመጣ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

አክለውም፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ የአዳራሽ ችግር አለ፡፡ በቂ አዳራሾች ባለመኖራቸው ጉባኤዎች በሚፈለገው ልክ ወደሀገራችን እየመጡ አይደሉም። በእነዚህ መሰረታዊ ክፍተቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ያጣችው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ቀላል አይደለም” ይላሉ አቶ ኪሩቤል፡፡

የሀገር ውስጥ ፍላጎቱም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ “ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ጉባኤ ያካሄዳሉ፡፡ እነዚህን ጉባኤዎች እራሱ የሚካሄዱበት ምቹ ቦታ አለ ብዬ አላምንም፡፡ እስከ አሁን በበቂ ደረጃ አልተዘጋጀም፡፡ ሆቴሎች በቂ አዳራሽ የላቸውም፡፡ 2 ሺህ ሰው የማስተናገድ አቅም ያላቸው አዳራሾችን የሚያቀርቡ ሆቴሎች ውስን ናቸው፡፡ ይህ ክፍተት የሀገርም የመዲናዋንም ኢኮኖሚ ጎድቷል” ብለዋል፡፡

ጆንሰን ኮንሳልቲንግ “How Convention Centers Catalyze Economic Growth” በሚል ርዕስ ያወጣው ፅሑፍ የኮንቬንሽን ማዕከላት በራሳቸው ከሚያስገኙት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ባሻገር ሌሎች ዘርፎችን በማነቃቃት ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርትን የማሳደግ ሚና እንደሚጫወቱ አስፍሯል። በተለይ ሀገራትን የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አብራርቷል፡፡

የኮንቬንሽን ማዕከላትን በቅጡ ያዘጋጁ ሀገራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ የሚለው ፅሑፉ፣ ይህም የማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ የተቃና እንዲሆን በማድረግ ለተጨማሪ ስራዎች የመነሳሳትን አዎንታዊ መንፈስ ያሳድራል ይላል፡፡

በኮንቬንሽን ማዕከላት አማካኝነት የሚፈጠር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለትምህርት እድል መስፋፋት፣ ለጤናው ዘርፍ መጠናከር፣ ለፈጠራ ክህሎት ማደግ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ መበራከት፣ ለፓርኮች ልማት፣ ለመሰረተ ልማት መረጋገጥ፣ ለመኖሪያ ቤቶች እጥረት መቀረፍ እና ለገቢ ምንጮች መስፋት ምክንያት በመሆን ለኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።

ታድያ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልም ኢትዮጵያ የንግድ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ዕድል በመፍጠር ከዘርፉ ላይ የሚገኘው ጥቅም ተጋሪ እንድትሆን ያስችላታል ማለት ነው፡፡ የማዕከሉ ዋነኛ ዓላማ ኤግዚቢሽኖችንና ጉባኤዎችን ማስተናገድ ቢሆንም ይህን የሚደግፉ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችና የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎችም አሉት፡፡

መዲናዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቅል ኢኮኖሚዋን የሚደግፉ የቱሪዝም ልማት ሥራዎችን በስፋት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ መካከል አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የመስቀል አደባባይ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት፣ አራት ኪሎ ፕላዛ፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽና ማዕከል እና ሌሎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ለማከናወን ተመራጭ እንድትሆን በር የሚከፍቱ ናቸው፡፡

በተካልኝ አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review