በአማራ ክልል “የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎች እና የነገ ተስፋዎች” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የማጠቃለያ የፓናል ውይይት መርሐ ግብር ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይረጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ጉዞው በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ከድሎች ጎን ለጎን በፖለቲከኞች፣ በልሂቃን እና በሌሎች የጋራ ተሳትፎ ወደ ፊት የሚስተካከሉ ጉድለቶች እንደነበሩም አንስተዋል።
ብልጽግና ከለውጡ በፊት የነበረውን ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ በማሸነፍ የመሐል ፖለቲካን ይዞ የመጣ ፓርቲ መኾኑንም ተናግረዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ አንድነትን፣ ወንድማችነትን እና እህታማማችነትን ይዞ የመጣ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል። ከሪፎርም እስከ ተቋም ግንባታ ድረስ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። እንደ ሀገር ነጻና እና ገለልተኛ ተቋማት መገንባታቸውንም ገልጸዋል። ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ተቋማትን ለመገንባት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
በሀገራዊ ለውጡ ቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፤ ሌሎች ታላላቅ ሥራዎችም ተከናውነዋል ብለዋል። የሕዳሴው ግድብ የተሠራበት መንገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ የመሪነት ጥበብ የታየበት መኾኑንም ገልጸዋል። የሕዳሴው ግድብ ሥራ ከለውጡ ስኬቶች መካከል አንደኛው መኾኑንም ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት የነበሩ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመፍታት መሥራቱንም ገልጸዋል። ከለውጡ ወዲህ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለአገልግሎት ዘርፉ እና ሌሎች ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ አንድነት ጉዟችን የሚያደናቅፍ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ አለ ያሉት ኀላፊው የጽንፈኝነት አሰተሳሰብ እና የዋልታ ረጋጥ ፖለቲካን ማክሰም እንደሚገባም አንስተዋል። በሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነትን ፣ መተሳሰብን እና አብሮነትን መሠረት ያደረገ እውነተኛ ትግል በመኖሩ ፈተናዎችን እያለፍን መጥተናል ነው ያሉት።
ግጭት ለሁሉም ሕዝብ እና አካባቢ እንደማይጠቅምም ተናግረዋል። ጽንፈኝነት የሕዝብን ባሕል እና እሴት የሚያወድም መኾኑንም ገልጸዋል። የሕዝብን መብት እና ጥቅም ለማስከበር በመተባበር የጽንፈኝነት አስተሳሰብን ማክሰም አለብን ነው ያሉት።
በመደጋገፍ እና በመተጋገዝ በተሠራው ሥራ ለውጥ ተገኝቷል ብለዋል። “በዚህ ዘመን የሚጠቅመው መደጋገፍ ነው፤ ለዚህ ጊዜ አብሮነት ነው የሚጠቅመው፣ ብሔራዊ አንድነት የፖለቲካ እሴትን መያዝ ነው የሚጠቅመው” ነው ያሉት።
ገዢ እና የወል ትርክት የሚባለውን የፖለቲካ እሳቤ ይዞ መሥራት ከፍላጎታችን ያደርሰናል ብለዋል። በጋራ መሥራት እና በጋራ ማደግ እንደሚገባ መናገራቸዉን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡