የወባ በሽታን ለመከላከል የጸረ-ወባ መድኃኒት አቅርቦት የማስፋት እንዲሁም የክትትል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል-የጤና ሚኒስቴር

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

የወባ በሽታን ለመከላከል የጸረ-ወባ መድኃኒት አቅርቦትን የማስፋትና ተጓዳኝ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤት አባላት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የወባ ወረርሽኝ ከመከላከል፣የመድኃኒት፣ የአጎበርና ሌሎች ግብዓቶችን ከማሰራጨት እንዲሁም አክሞ ከማዳን አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ሰፊ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና አክሞ ለማዳን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በምላሻቸው ዘርዝረዋል።

በዚህም ከክልሎች ጋር በመተባበር በቅኝት፣በመከላከል፣ በመድኃኒት ሥርጭትና አክሞ በማዳን የተከናወኑ ተግባራትን አስረድተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ8 ሚሊዮን በላይ የጸረ-ወባ መድኃኒትና ከ6 ሚሊዮን በላይ ፈጣን የመመርመሪያ ኪት መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበር መሰራጨቱንም ጠቅሰዋል።

በቤት ለቤት ልየታ ከ2 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራዎችን በመለየት የትኩሳት ምልክት ያሳዩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

የተሰራጩ መድኃኒቶች በትክክል ኅብረተሰቡ ጋር መድረሳቸውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ኅብረተሰቡ መድኃኒትና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ እንዲጠቀም ማስገንዘባቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

All reactions:

3939

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review