የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል -ጤና ሚኒስቴር

AMN – ጥቅምት 14/ 2017 ዓ.ም

የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስገነዘቡ።

ሚኒስቴሩ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር እየተከናወነ ያለውን ስራ በሚመለከት ሳምንታዊ የግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡

በመርሐ-ግብሩም የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልእክት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወቅታዊ የወባ ወረርሽኝን በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ክላስተሮች ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቆጣጣር አንጻር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በመገምገም ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ይሁን እንጅ ከክረምት መዉጣት ጋር ተያይዞ የወባ በሽታ እየጨመረ በመሆኑ፤ ወረርሽኙን ለመግታት በየደረጃዉ ያለዉ አመራር፣ የጤና ባለሙያና የሚመለከተዉ ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ወርሽኙን ለመግታት እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ያነሱት ሚኒስትሯ በተለይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በዕቅድ መስራት ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የቅኝትና የቁጥጥር ስራን ማጠናከር፣ በቤት ለቤት ስራ ማህበረሰቡን በማንቃትና በማደራጀት አከባቢዉን እንዲያጸዱ፣ ዉኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና ለወባ መራባት ምቹ የሆኑ ረግረጋማ አከባቢዎችን የማዳፈን ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለዚህም በየደረጃዉ ያለዉ አመራር ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አከላት ጋር በመሆን ህብረተሰቡ በተደራጀ መልኩ በማሳተፍ ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ማመላከታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

መድሃኒት እና የግብዓት አቅርቦት ላይ ያለውን ስርጭት በተመለከተም ተገቢው ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት የስራ መመሪያ እና አቅጣጫ በመስጠት ለባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ተገቢውን ስራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review