AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም
ላለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም የኮሪደር ልማት አስተባባሪዎች ጋር በመሆን በ2ኛ ምዕራፍ በከተማችን እየለሙ የሚገኙ ስምንት ኮሪደሮችን የስራ አፈጻጸም ተዘዋውረን ገምግመናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
“በጉብኝታችንም ወቅትም የወንዞችን ብክለት በመከላከል ጽዱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ለመፍጠር የብክለት መከላከል ህግን ህብረተሰባችን መቀበሉን እና እየተገበረዉ መሆኑን ተመልክተናል” ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለፁት፣ የ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ 135 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው የመንገድ ግንባታ፣ 42 ኪ.ሜ የሚረዝም የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ እና 431 ሄክታር የሚሸፍን የአረንጏዴ ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ስርዓት ለማዘመን ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ 23,320 በላይ መኪኖችን የማስቆም አቅም ያለው የፓርኪንግና ተርሚናሎች ግንባታ፣ 112 የህዝብ የመጸዳጃ ቦታዎች ግንባታ እንዲሁም 2669 ህንጻዎች እድሳት እየተከናወነ እንደሚገኝም ከንቲባዋ አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም የህጻናት መጫወቻ ሜዳዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን ያካተተ ከ 62 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ የስራ እድልን የፈጠረ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አክለውም፣ ከተማውን በመበከል የህዝቡን ጤና በመጉዳት ከፍተኛ አሉታዊ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩትን ህግ እና ስርዓት አዉጥተን የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ እየተገበርን ነዉ ብለዋል።
በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ያልገነቡ እና የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓታቸውን ያላስተካከሉትን በመቅጣት ላይ እንገኛለን ያሉት ከንቲባዋ “ከቅጣቱ በላይ የምንፈልገው ህዝባችን በዋናነት ለራሱ ጤና ሲል የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቱን እና ብክለት መከላከልን እንዲተገብር በመሆኑ ሁላችንም ለዚህ ርብርብ እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል”::
“ያቀረብንላቸውን ጥሪ በመቀበል ህንጻዎችን በማደስ፣ ቀለም በመቀየር እና በከተማዋ ስታንዳርድ መሰረት መብራት በመዘርጋት እያገዙን የሚገኙ የከተማችን ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም የመንግስትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ሙያዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ እያደረጉልን የሚገኙ ነዋሪዎቻችንን በራሴ እና በከተማ አስተዳደራችን ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ” ሲሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
“በቀሪ ጊዜያት ልዩ ክትትል በማድረግ ቶሎ መጠናቅ ያለባቸውን ስራዎች መጨረስ፣ መደገፍ የሚገባቸውን ደግሞ እየደገፍን ህዝባችንን በታማኝነት ለማገልገል በገባነው ቃል መሰረት 2ኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አጠናቅቀን ለአገልጋሎት ክፍት የምናደርግ ይሆናል” ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡