AMN-ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በህገ ወጥ መንገድ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ባደረጉ 2ሺ 311 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በኦፕሬሽን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ እንደተነገረው እነዚህ የንግድ ተቋማት ምርት በመጋዘን የደበቁ፣ያለ ንግድ ፍቃድ ሲነግዱ የተገኙና ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ላይ ዋጋ ጨምረው የሸጡ ናቸው ተብሏል።
በሩብ ዓመቱ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ በተደረገ የኦፕሬሽን ስራ 4ሺ 075 ዶላር፣ 3 መቶ ሀሰተኛ ዶላር፣ 19 ሺ 600 የኢትዮጵያ ብር፣51 ሺህ 550 ሀሰተኛ የኢትዮጵያ ብር፣ 1ሺ 550 ህገወጥ ዩሮና 190 ህገወጥ ፓውንድ ገንዘቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ስለመቻሉም ተነስቷል።
ከሀሰተኛ ሰነድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ 25 የተለያዩ ፓስፖርቶች፣14 ሀሰተኛ መታወቂያ እንዲሁም ህገወጥ የቦታ ካርታ በማዘጋጀት ለማጭበርበር የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉም ተነግሯል።
በአጠቃላይ በነዚህ ጊዜአት ወንጀልን በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የወንጀል ምጣኔ እንዲቀንስም አድርገዋል ተብሏል።
በትዕግሥት መንግሥቱ