የውሃ ጋኖቹ ቁልፎች

ተፈጥሮ ቸርና ለጋስ ናት፤ በአግባቡ ከጠበቅናትና ከተንከባከብናት የምንበላውን፣ የምንጠጣውን፣ የምናመርተውን፣ ለተለያየ አገልግሎት የምንጠቀምበትን ውሃ እንዲሁም የምንተነፍሰው አየር ትሰጠናለች፡፡ በተቃራኒው ካጎሳቆልናት በህይወት ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን ታሳጣናለች፡፡

የሰው ልጅ በምድር ላይ ለመኖር የአፈር፣ ዕፅዋት፣ እንስሳት፣ ውሃ፣ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች መኖርና ጤናማ መስተጋብር ያስፈልገዋል፡፡ ከእነዚህ ለህይወት መቀጠል መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች የአንዱ መጉደል ለምሳሌ፡- የዕፅዋት ወይም የውሃ መጥፋት የተፈጥሮ ሚዛንን በማዛባት የሰው ልጅ ህልውናን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡

የአረንጓዴ አሻራው የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው

በከተሞች ከህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ፈጣን እድገት፣ የዕፅዋት ሽፋን መመናመን፣ የአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ የአሁኑና የወደፊት ትውልድ የሚያስፈልገውን ንጹህ፣ ጥራት ያለውና በቂ ውሃ የማቅረብ ጉዳይ ትልቅ ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ማእከል፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች መኖሪያም ናት፡፡ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ለመጠጥ፣ ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪና ለተለያዩ አገልግሎት የሚያስፈልገውን ውሃ ከከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ ምንጮች እያቀረበች ትገኛለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከከርሰ ምድር እና ገፀ ምድር የውሃ መገኛዎች በቀን 792 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ውሃ እየተመረተ ይገኛል፡፡ የከተማዋን ነዋሪዎች የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ሰፊ የሆነ አለመጣጣም እንዳለ እንደሚያሳይ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

የከተማዋን ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግና ለማርካት አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባሻገር አሁን ላይ ውሃ እያመነጩ ያሉ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ ምንጮች የሚጠበቅባቸውን ያህል ውሃ ማመንጨት እንዲችሉና አቅማቸው እንዲጎለብት የተፈጥሮ እንክብካቤና ጥበቃ ስራ ማከናወን የግድ ይላል፡፡ ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዚህ ረገድ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አይነተኛ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በዋናነት ከከተማዋ ፈጣን እድገት ጋር የሚመጣጠን ንፁህ ውሃ ማቅረብ እና በተለያየ መልኩ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎት የመስጠት ተልዕኮን በመያዝ እየሰራ ይገኛል። ተቋሙ እነዚህን ስራዎች ሲያከናውን የውሃ መገኛ ተፋሰሶችን መንከባከብና መጠበቅ እንደ አንድ ቁልፍ ተግባር በመያዝ የውሃ መገኛ ተፋሰሶች አስተዳደርና ጥበቃን የሚመለከት ራሱን የቻለ ዲቪዥን በማደራጀት እየሰራ እንደሚገኝ በባለስልጣኑ የውሃ መገኛ ተፋሰሶች አስተዳደርና ጥበቃ ዲቪዥን የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታየ ያብራራሉ፡፡

ለከተማዋ ከሚቀርበው ውሃ ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ከከርሰ ምድር ውስጥ ከጥልቅ ጉድጓዶች የሚወጣ ነው፡፡ ቀሪው ከገፀ ምድር የውሃ ምንጮች የሚገኝ ነው፡፡ የለገዳዲ፣ የድሬና የገፈርሳ ተፋሰሶች ዋነኛ የገፀ-ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ መገኛ አካባቢዎች ናቸው፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደገለፁት፤ የስራ ክፍሉ ከሦስት ዓመት በፊት ከተደራጀ በኋላ በውሃ መገኛ ተፋሰሶች አካባቢ የተለያዩ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ አንደኛ በውሃ መገኛ ተፋሰሶች ላይ እየተሰራ ያለው የደን ሽፋንን ከፍ ለማድረግ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት 50 ሺህ እና ባለፈው ዓመት 150 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በያዝነው ዓመት ደግሞ 175 ሺህ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ፀድቀዋል። ይህም በተፋሰሱ ያለውን እርጥብ አየር ለመጨመር፣ ድርቅንና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ያግዛል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ስራ ካልተሰራ አፈሩ እየተሸረሸረ፣ የሚዘንበው ዝናብ ወደ መሬት ከመስረግ ይልቅ ጎርፍ ሆኖ ስለሚሄድ የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች በደለል እንዲሞሉና ውሃ እንዳያመነጩ ያደርጋቸዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ጉድጓዶች ውሃ የማመንጨት አቅማቸው እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡

የአፈር መሸርሸር ሲኖር ጎርፍ ሆኖ የሚሄደው ውሃ በታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ ጥፋቶችን ያስከትላል፡፡ ይህንን ለመከላከል የችግኝ ተከላው በዋናነት በግድቦች መገኛ አካባቢ አተኩሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው አቶ ሙሉጌታ የሚያስረዱት፡፡

ባለስልጣኑ ከከተማዋ የአስተዳደር ወሰን ውጪ ከሚያከናውነው የችግኝ ተከላ ባለፈ በከተማዋ ውስጥ እንደ አቃቂ ቃሊቲ፣ አራብሳ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችና አስር በሚሆኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ በማከናወን የከተማዋን የደን ሽፋን ለመጨመር እየሰራ ይገኛል፡፡

ሌላው አፈር እንዳይሸረሸር እና ውሃው ጎርፍ ሆኖ እንዳይወርድ የሚከላከሉ የእርከን ስራ፣ በሽቦ ጥልፍ ማጠር (ጋቢዮን)፣ ውሃ የሚይዙ ትናንሽ ጉድጓዶችን መቆፈርና መሰል  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የአፈር ክለት ባለባቸው አካባቢዎች ከ600 ሄክታር በላይ የሆነ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም ወደ ግድቦች የሚገባውን የደለል መጠን መቀነስ እንደተቻለ አቶ ሙሉጌታ ያስረዳሉ፡፡

በውሃ መገኛ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም የውሃ ግድብ ሲሰራ እየተፈናቀለ ውሃን ሲሄድ ከማየት በስተቀር ተጠቃሚ እንዳልነበር ያነሱት አቶ ሙሉጌታ፤ የችግኝ ተከላውና የአካባቢ ጥበቃው ዘላቂነት እንዲኖረው ማህበረሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍበት የደን ዕፅዋትን ብቻ ሳይሆን የፍራፍሬ ችግኞችንም ጭምር በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡ በለገዳዲ ተፋሰስ በ10 ሄክታር መሬት ላይ እንደ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ አፕል፣ ሮማን፣ ዘይቱና… ያሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የፍራፍሬ ዛፍ ደን መፍጠር ተችሏል፡፡

ማህበረሰቡ ውሃ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ 109 አባላትን ያቀፉ ሰባት ማህበራትን በማደራጀት የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። የአካባቢው ማህበረሰብ በተለምዶ እንደ ጤፍ፣ ገብስ ያሉ ሰብሎችን በማምረት ኑሮውን የሚመራ ሲሆን፤ እነዚህ ሰብሎች ሲዘሩ ደጋግሞ ማረስ የሚጠይቁ በመሆናቸው ለደንና አፈር መሸርሸር ምክንያት ይሆናሉ። የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል ግን አፈር እና ውሃን ለመጠበቅ ከማገዙም ባሻገር ማህበረሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅ፣ በጓሮው ጭምር በመትከልና በገበያ በመሸጥ በዘላቂነት ኑሮውን የሚደጉምበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡

አዲስ አበባን ውሃ የሚያጠጡ የውሃ ምንጮች ከከተማዋ የአስተዳደር ክልል ውጪ በሸገር ከተማ ኩራ ጅዳ፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩ እና ገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተሞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አካባቢዎች  የመንከባከብና የመጠበቅ ስራ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በሸገር ከተማ አስተዳደር እና በስሩ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አስተዳደር አካላት፣ ማህበረሰብ፣ የፌዴራል ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ቪተንስ ኢቪደንስ ኢንተርናሽናል ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ሙሉጌታ የነገሩን።

በአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስ እና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ መንግስቱ በበኩላቸው ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ ከተማ ከእንጦጦ ተራራ ጀምሮ በተከናወነው የችግኝ ተከላ ጎርፍ ሆኖ የሚመጣውን ውሃና ደለል መቀነስ ተችሏል፡፡ ገላጣ የነበሩ ቦታዎች ላይ ችግኞች በመተከላቸው በቅርብ ርቀት ምንጮች ተፈጥረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች አንዱ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ነው። ከዓመታት በፊት ከድል በር እስከ ሳንሱሲ የሚደርሰውና 705 ሄክታር የሚሸፍነው ይህ ማዕከል በባህር ዛፍ ዕፅዋት የተሸፈነ ነበር። ባለፉት ዓመታት አካባቢው ላይ የነበረው ባህርዛፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከማዕከሉ እንዲወገድ በማድረግ ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆኑ ሀገር በቀል ዕፅዋት ተተክለውበታል። የተጎዳው ተራራ ላይ ውሃ መያዝ የሚችሉ ትናንሽ ጉድጓዶች፣ እርከን፣ የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መሰራቱን በማዕከሉ የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ ማሞ ያስረዳሉ፡፡

በዚህም ከማዕከሉ የሚፈልቁ ከአራት በላይ የወንዝ ምንጮች አቅም እየጎለበተ መጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከሚያቀርበው ውሃ በተጨማሪ በኩሬ ውሃ በማቆርና ጉድጓድ በመቆፈር ከከርሰ ምድር ዓመቱን ሙሉ ጥቅም ላይ የሚውል ውሃ ማግኘት ተችሏል፡፡

     ቀጣይ ምን መሰራት አለበት?

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ መገኛ ተፋሰሶች ጥበቃና አስተዳደር ዲቪዥን ኃላፊ አቶ መሉጌታ እንደሚናገሩት፤ የውሃ መገኛ ተፋሰሶችና ግድቦች መገኛዎች በዕፅዋት እንዲሸፈኑ ከማድረግ አኳያ እስከአሁን የተሰራው ስራ በቂ አይደለም፡፡ ግድቦቹ ረጃጅም ጅረቶች ስለሆኑ እነሱን ተከትሎ በሰፊው ችግኝ መትከል፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ማከናወን ይጠይቃል፡፡ በከተማዋ ውስጥ የሚሰራው እንዳለ ሆኖ በውሃ መገኛ ተፋሰሶች ላይ የችግኝ ተከላ በማከናወን ረገድ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ተቀናጅተው ከመስራት አንጻር ክፍተት ይታያል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በአንድ ክልል  የሚወሰኑ ሳይሆኑ አንዱ ከአንዱ ጋር የተሳሰሩ፣ ከክልል፣ ከሀገር አልፎ አለምአቀፋዊ ትብብር የሚሹ እንደሆኑ ያነሳሉ። 

ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክሩት በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ፣ በአዲስ አበባ ብቻ በሚሰራው ስራ በዘላቂነት የውሃ አቅርቦትን ማረጋገጥ ስለማይቻል በከተማዋ ዙሪያ በእርሻ አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በደንብ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ክልልና የክልሉ አካል በሆነው የሸገር ከተማ አስተዳደር ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የለገዳዲና ድሬ ተፋሰሶች ብቻ 280 ሺህ ስኬዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ይሸፍናሉ፡፡ በውስጣቸውም በተለያየ አቅጣጫ ወደ ግድቡ ውሃ ይዘው የሚመጡ በርካታ ጥቃቅን ተፋሰሶች የሚገኙ ሲሆን፤ የችግኝ ተከላው፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃው የት ላይ ቢሰራ ውጤታማ ይሆናል? የሚለውን ልምድ በመቀመር እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሙሉጌታ ያነሳሉ፡፡

የአዲስ አበባን ውሃ ሽፋን ለመጨመር ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡ ሊሰሩ በዕቅድ የተያዙ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት መመለስ የሚቻል ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር ቀደም ብለው የተሰሩ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውሃ የማመንጨት አቅማቸው እንዳይዳከምና እንዲጎለብት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

“አብዛኛው ሰው ውሃን የሚያውቀው ቧንቧ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን የውሃ ምንጩ ካልተጠበቀ ቧንቧ ላይ የሚመጣ ውሃ ሊኖር አይችልም፡፡” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ የውሃ ምንጮችን መጠበቅና መንከባከብ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግስት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል መምህርና ተመራማሪ መኩሪያ አርጋው (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የችግኝ ተከላ ከከተማዋ ወጣ ባሉ ተራራማ አካባቢዎች መከናወን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ተራራዎች የኑሮ መሰረት በመሆናቸው የችግኝ ተከላው የተራቆቱ ተራራዎችን ደን ማልበስ ላይም ያተኮረ መሆን አለበት፡፡

ተራራ ውሃን አንደርድሮ በፍጥነት ሜዳው ላይ የሚያደርስ ሲሆን፤ ውሃው ፍጥነቱንና ሃይሉን በመቀነስ ወደ ከርሰ ምድር እንዲገባ ካልተደረገ አፈሩ በመሸርሸር የእርሻ መሬቶችን ያጠፋል፤ ጎርፍ ይፈጥራል። ተራራውን በደን ማልበስ ከተቻለ ግን ውሃን ወደ ከርሰ ምድር በማስገባት በበጋ ወቅትም ቆፍሮ መጠቀም ይቻላል፡፡

የግድቦቹን ህይወት ማርዘም የሚቻለው ተራራማ አካባቢዎች በደንና በዛፍ ሲሸፈኑ ነው፡፡ አሁን ላይ ሲታይ ተራሮቹ በበቂ ሁኔታ በዛፎች የተሸፈኑ አይደሉም፡፡ ተራራማ ቦታዎች በአግባቡ በዛፍ ካልተሸፈኑ የከርሰ ምድር ጉድጓዶች የውሃ መጠናቸውን እየቀነሰ ሊመጣ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡

መኩሪያ (ፕሮፌሰር) እንደሚያስረዱት፤ በተራራማ ቦታዎች የሚተከሉ ሀገር በቀል ዕፅዋቶች ምን ዓይነት ናቸው? በእርሻ መሬቶች ላይ ምን ዓይነት የፍራፍሬ ዛፎች መተከል አለባቸው? የሚለውን በማጥናት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በግድቦች ዙሪያ ያሉት ቦታዎችም ዙሪያቸውን በቁጥቋጦ፣ በሳርና በዛፍ መሸፈን ይኖርበታል፡፡ 

በጥቅሉ ያለ ችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ ቀጣይነት ያለው የውሃ አቅርቦትን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ የአረንጓዴ አሻራው የአዲስ አበባን የውሃ አቅርቦት ዘላቂነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን በውሃ መገኛ ተፋሰሶችና ግድቦች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ይገባል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review