የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ደረጃ የማሻሻል ጥረት

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከተማዋ የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖራት እና ሁሉንም ህብረተሰብ ተደራሽ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ የመንገድ አውታር ዝርጋታ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ባለስልጣኑ የሚያከናውነው የመንገድ ግንባታ ስራዎች በሶስት ምድብ ሊመደቡ ይችላሉ፡-  አንደኛ የነባር መንገዶችን ደረጃ ለማሻሻል ዓላማ የሚገነቡ (ማለትም በጥራት፣ ተሸከርካሪ በማስተናገድ አቅም፣ አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴን ከማበረታታት፣ ለእግረኞች ምቹ ከማድረግ፣ ትራክ ከማሳለጥ፣ምሉዕ የከተማ ጎዳና  ፅንሰ ሀሳብን ከማካተት … ወዘተ)

ሁለተኛ ምንም ዓይነት የመንገድ መሰረተ ልማት የሌላቸውን አካባቢዎች (በተለይ አዳዲስ የመኖሪያ አካባቢዎችን )  የመንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚገነቡ ፡፡

ሶስተኛ አቋራጭ መንገዶችን በመገንባት የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ እና በከተማ ውስጥ በጉዞ የሚጠፋውን ጊዜ እና የሚቃጠለውን ነዳጅ መቀነስ የሚያስችሉ መንገዶች ግንባታ ይገኝበታል፡፡  በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በዋና ዋና መንገዶች ላይ ይፈጠር የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ማቃለላቸው በማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 ሁሉም አይነት የመንገድ ልማት ስራችን  ድምር ውጤት የመንገድ መረቡን በማሳደግ አዲስ አበባን የተሻሻለ የመንገድ ትራንስፖርት ስርዓት ባለቤት፣  ጤናማ የትራፊክ ፍሰት ያላት እና ለኑሮ ተስማሚ ከተማ ማድረግ  ነው፡፡

ከቱሉ ዲምቱ ቀለበት መንገድ ድረስ የተሰራው የውስጥ ለውስጥ መንገድ

ይህም ምሉዕና ተደራሽ የመንገድ መሠረተ ልማት በማቅረብና በመንከባከብ መዲናችንን በ2022 ከአፍሪካ 5 ተመራጭ ከተሞች አንዷ ለማድረግ ያነገብነው ራዕይ አካል ነው፡፡ 

ባለሥልጣኑ በዚህ አግባብ ከከተማ አስተዳደሩ በሚመደብ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ለዛሬ በቅርብ ዓመታት ተጀምረው ባሳለፍነው 2016 በጀት ዓመት ከተጠናቀቁና አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 3ቱን ለዋቢነት እንዳስሳለን።

አውጉስታ – ወይራ መንገድ ፕሮጀክት

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ያለባቸውን ዋና ዋና ቦታዎች በጥናት በመለየት በርካታ አቋራጭና አማራጭ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ገንብቶ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት እያደረገ ይገኛል፡፡

ከአጉስታ ወይራ ሰፈር የተሰራው የውስጥ ለውስጥ መንገድ በከፊል

ከእነዚህም መካከል በተለምዶ አውግስታ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እስከ ወይራ ሰፈር ድረስ የተገነባው የአስፋልት መንገድ አንዱ ነው፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ 1.5 ኪ.ሜ ርዝመት እና 25 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን አሁን ላይ 97.6 በመቶ ተጠናቆ የትራፊክ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የመንገዱ ግንባታ መጠናቀቅ በመቻሉ ከጦር ሀይሎች ወደ ቶታል በሚወስደው የውጪ ቀለበት መንገዱን በመያዝ በአውግስታ ወደ ቀኝ በመታጠፍ  ወደ ወይራና ቤተል የሚደረገውን የጉዞ ጊዜ እንዲያጥር አድርጎታል፡፡

የቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚኒየም የውጭ ቀለበት መንገድ ፕሮጀክት

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በስራ ተቋራጮች እያስገነባቸው ከሚገኙ በርካታ አቋራጭ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚኒየም – የውጨኛው ቀለበት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሌላኛው ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 1.4 ኪ.ሜ ርዝመት እና 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን አሁን ላይ የአስፋልት ማንጠፍ፣ የእግረኛ፣ የመንገድ ዳር መብራት ፖል ተከላ እና የቀለም ቅብ ስራዎች ተጠናቀው የትራፊክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የግንባታ ስራውን ዲሪባ ደፈረሻ የተባለ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ ከ185.5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ያከናወነው ሲሆን የማማከርና የግንባታ ቁጥጥሩን ስራ ደግሞ ጎንድዋና አማካሪ ድርጀት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡

የፈረንሳይ ኤምባሲ- አቦ ቤተክርስቲያን መንገድ ፕሮጀክት

ልክ ከ6 ኪሎ አደባባይ እንደተነሱ ወደ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አቅጣጫ ሲጓዙ በተለምዶ 05 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን ቃኘው ሻለቃ አደባባይን እንዳለፉ ከፈረንሳይ ኤምባሲ ዋናው በር መግቢያ ዝቅ ብሎ ወደ ቀኝ በመታጠፍ መነሻውን ያደረገ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ይገኛል፡፡

ይህ የፈረንሳይ ኤምባሲ- ፈረንሳይ ፓርክ -አቦ ቤተክርስቲያን የመንገድ ግንባታ ቃኘው ሻለቃ አደባባይ ሆኖ አሻግሮ ሲመለከቱ እንደ ሳር ውስጥ መንገድ በርቀት በቀጭኑ ይታያል። ከዚህ በፊት በቦታው አስፋልት መንገድ አልነበረም፤የአካባቢው ነዋሪዎችም በተለይ አቦ ቤተክርስቲያን እና አካባቢው የሚኖሩ ከተሜዎች ወደ መሀል ከተማ ለመምጣት ከፍተኛ 12 የሚገኘው ፈረንሳይ ማዞሪያ ድረስ የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

አሁን ግን 1.2 ኪ.ሜ ርዝመትና 15 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ፣ የመንገድ ዳር መብራትና የእግረኛ መንገድ የተሟላለት ባለ አንድ አቅጣጫ የአስፋልት መንገድ በመገንባቱ ችግራቸው ተረት ሆኖ ቀርቷ፡፡ ‹‹ልጁን አንሺው ምጡን እርሺው>> ይባል የለ:: የክረምቱን ጭቃ፣ የበጋውን ፀሀይ፣ ሌላው ቀርቶ ወላድ ምጥ ሲይዛት እንኳ የአምቡላንስ መንገድ እጦታቸውን ረስተው ዛሬ ላይ ታክሲው ከበራቸው ላይ ቆሞ አራት ኪሎ… 6 ኪሎ… የሞላ፣ የሞላ አንድ ሰው እያለ ሲጣራ ወይ ጊዜ— ጊዜ ደጉ ያስብላል፡፡

አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከ6 ኪሎ እና ከሌሎች ቦታዎች ተነስተው ወደ ፈረንሳይ ፓርክ፣ ፈረንሳይ አቦ ቤተክርስቲያን እና አልፈው ወደ ጉራራ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ለሚጓዙ አሽከርካሪዎች አማራጭና አቋራጭ መንገድ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በ2016 በጀት ዓመት 1 ሺ አንድ መቶ አርባ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ የመንገድ ግንባታ እና የጥገና ስራዎችን ከማከናወኑም በላይ 25.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ከ 8 እስከ 30 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያላቸው 11 የመንገድ ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review