ከተጠባቂው ጉባኤ

You are currently viewing ከተጠባቂው ጉባኤ

“የውስጥ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ የሚል እምነት አለኝ”-የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ሰለሞን ተፈራ

ወቅቱ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች የተወጠረችበት ነበር፡፡ ባህር ላይ ሆና ወጀብ እንደሚያናውጣት መርከብ አካሄድና መዳረሻዋን መገመት ያስቸግር ነበር፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የለውጥ ድምፆች ከፍ ብለው ይስተጋቡ ነበር፤ በተለይ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት፡፡

በተጠራቀመ የህዝብ ብሶት እና በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውስጥ በነበረ ሀይል ግፊት ሀገራዊ ለውጡ መጣ፡፡ ለውጡ ወደ ገደል አፋፍ እየተንደረደረች ለነበረችው ሀገር ከፍተኛ ተስፋን የፈነጠቀና ያለውን ውጥረት ማርገብ የቻለ ነበር፡፡

ለውጡን ተከትሎ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በፖለቲካው መስክ ከመጡ ለውጦች መካከል ገዢው ፓርቲ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከስሞ ውህድ የሆነው የብልፅግና ፓርቲ ውልደት ይጠቀሳል፡፡

በኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ የመወሰን ስልጣን ያላቸውና የሌላቸው፣ አባል እና አጋር ፓርቲዎች የሚል ክፍፍል ነበር፡፡ አባል የሆኑ የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የመወሰን ስልጣን ሲኖራቸው፣ ከእነዚህ ውጪ የነበሩት አምስቱ ክልሎች “አጋር” በሚል የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ፣ በከፍተኛ የአመራር ኃላፊነት የመምረጥና መመረጥ መብት አልነበራቸውም፡፡ ይህም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ መስክ መገለልና ብሶት እንዲፈጠር በማድረግ የብልፅግና ፓርቲ እንዲወለድ ምክንያት እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞን ተፈራ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ህዳር ወር 2012 ዓ.ም ግንባር የነበረው ድርጅት እንዲከስም ተደርጎ አንድ ውህድ የሆነ የብልፅግና ፓርቲ ተፈጠረ፡፡ ይህም ሲባል ተገልለውና የዳር ተመልካች ሆነው የቆዩ ክልሎችን ጨምሮ ሁሉም በሀገር ጉዳይ በባለቤትነት የመወሰን መብትን ያጎናፀፈና የሀገር አንድነትን ማጠናከር የተቻለበት ሁኔታ መፍጠሩን አቶ ሰለሞን ያነሳሉ፡፡

ፓርቲው ከተመሰረተ በኋላ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 4 ቀን  2014 ዓ.ም ነበር ያካሄደው፡፡ በወቅቱም የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ ዘላቂ ሰላምን እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት የሚያስችለው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን መደገፍ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ሀገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደነበር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ከሰሞኑ ከሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡

ሁለተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን እያካሄደ እስካለበት ጊዜ ድረስም ፓርቲው በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች በርካታ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በኢትዮጵያ ችግሮችን በመነጋገር፣ በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህል እንዲዳብርና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚያስችለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ኮሚሽን እንዲቋቋም በማድረግ ገዥው ፓርቲ ትልቅ ድርሻ መወጣቱን የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በፓርቲው ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡

ፓርቲው በአባላት ቁጥርም ከፍተኛ እድገት አሳይቷል፡፡ ሲቋቋም 8 ሚሊዮን አካባቢ አባላት የነበሩት ሲሆን፤ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይህም ከፓርቲው የሀሳብ ጥራት፣ ሚዛናዊ እይታ፣ እሳቤው አንዱን ወዳጅ ሌላውን ጠላት የማያደርግ፣ አብሮ መኖርን፣ እህትማማችነትና ወንድማማችነትን የሚጋብዝ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ  የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ለኤ.ኤም.ኤን ተናግረዋል፡፡

በፓርቲው መሪነት በኢኮኖሚ መስክ በሀገር በቀል እሳቤ በተከታታይ 7 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል። በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል፣ የወጪ ንግድ እና ተኪ ምርትን በማሳደግ፣ በሰው ተኮርና በጎ ፈቃድ ስራዎች፣ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ በሽታዎችን በመከላከልና የማከም አቅምን በማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ጉባኤውን አስመልክቶ ከሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡

በዲፕሎማሲውም በዜጋና ሀገር ተኮር፣ ወዳጅን የማብዛት ዲፕሎማሲ በመከተል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ኢትዮጵያ የ“ብሪክስ ፕላስ” የተሰኘውን የትብብር ቡድን መቀላቀሏ ለዚህ ተጠቃሽ ምስክር እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞንም ይህን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ በገዥው ፓርቲ መሪነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በእኩል የሚሳተፉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ በተለይ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን በማልማትና በመጠቀም ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የተሰራበት፣ ይህ የኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ጥያቄው ህጋዊነት ያለው መሆኑን የተረዳበት ሁኔታ መፈጠሩን ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡ 

2ኛው ጉባኤና የሚጠበቀው ውሳኔ ብልፅግና ፓርቲ 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን አባላትን ማፍራት የቻለ በዓለም በግዙፍነት ከሚጠሩ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፤ እስከ ነገም ይቀጥላል፡፡

በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ የፓርቲው ፕሮግራም፣ ደንብ፣ ያለፈው ጉባኤ ውሳኔና አቅጣጫዎች አፈፃፀም የሚገመገሙበት፣ ማሻሻያዎች የሚፀድቁበት፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ሊያሳካ የሚያስባቸው ውጤቶች አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንዲሁም እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚመረጡበት ወሳኝ መድረክ ነው፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የኢንስፔክሽንና ሥነ ምግባር ኮሚሽን አባላት፣ የፓርቲው የተለያዩ አደረጃጀቶችን የሚወክሉ በድምሩ 1 ሺህ 700 ሰዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የውጭ ሀገራት እህት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተጋባዥነት እንደሚሳተፉበት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ከጉባኤው በፊት ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት መረጃ ይጠቁማል፡፡

በጉባኤ የሚወሰኑ ውሳኔዎችና የሚቀመጡ አቅጣጫዎች በሀገሪቱ ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያላቸው እንደሆኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አደም አንስተዋል፡፡ ሀገርን የሚመራ ግዙፍ ፓርቲ የሚያካሄደው ጉባኤ እንደመሆኑ የሚጠበቅ ነው ያሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞን፣ በተለይ በሀገር ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያስቀጥሉ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

“የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አጀንዳ በማድረግና በዲፕሎማሲው ጠንክሮ በመሰራቱ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥያቄው ተገቢነት እንዳለው መግባባት ተፈጥሯል። በጉባኤውም አጀንዳው በእቅድ ተይዞ፣ በጥልቀትና በበሳል ዲፕሎማሲ ወደፊት እንዲራመድ ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡” ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰለሞን ከጉባኤው የሚጠብቁትን ያነሳሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት የጋራ ትርክትን ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ ነበር፡፡ በጉባኤውም በታሪክ ትርክት፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎች በሀገራዊ ምክክርና በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ውሳኔዎች ይኖራሉ ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ፡፡

ሌላው ባለፉት ዓመታት ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ በመውሰድ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት በተሰራው ስራ ሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች መጥታለች፡፡ እነዚህ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድም የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ በጥልቀት ውይይት በማድረግ በተጠናከረ መንገድ የሚሰራበትን ሁኔታ አቅጣጫ ይቀመጣል፡፡ የተገኙ ድሎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት፤ ያጋጠሙ ችግሮች የሚታረሙበት፣ ብልሹ አሰራር ላይ የሚሳተፉ አመራሮች ላይ እርምጃ የሚወሰድበት፣ የስልጣን ሽግሽግ የሚደረግበት ጉባኤ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡   

ከሰላምና መረጋጋት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች ሲንከባለሉ የመጡ፣ የአግላይና የነጠላ ትርክት ፖለቲካ ማራመድ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ በጉባኤውም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ጥያቄ ያላቸው አካላት፣ ነፍጥ ያነሱ ሀይሎች ነፍጣቸውን አስቀምጠው ወደ ብሔራዊ ምክክር የሚመጡበትና በሀገራቸው ጉዳይ በባለቤትነት የሚሳተፉበትና ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ውሳኔ ይተላለፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ሰለሞን ያነሳሉ፡፡

የኢትዮጵያን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ለማስጠበቅ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያም የፖለቲካ ጥያቄዎችን በፖለቲካዊ ንግግር ለመፍታት የሚያስችል ጠንከር ያለ ውሳኔ ያስተላልፋል ብለው እንደሚጠብቁም አክለው ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት፣ ከጉባኤው ፓርቲውን እና መንግስትን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ይወሰናሉ ተብሎ ይጠበቃል። አንደኛ በፓርቲው ውስጥ በአመራር፣ በአደረጃጀትና አሰራር፣ የአመለካከትና አስተሳሰብ አንድነት ለማምጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ፡፡ ሁለተኛው በፓርቲ መሪነት መንግስት የጀመራቸውን የተቋም ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ፣ የተቀረጹ የተለያዩ የልማት ተነሳሽነቶች ዘላቂነትና ባህል ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያበረታቱ በጥቅሉ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review