የመስቀል ደመራ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ከማይዳሰሱ ቅርሶች እና የአደባባይ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በየዓመቱ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ህዝብ በተገኘበት በድምቀት ይከበራል፡፡ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚመጡ እንግዶች የሚታደሙበት በዓል መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎች ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡
ሱዚ ባርቴዝ
ሱዚ ባርቴዝ አሜሪካዊ ዜግነት አለው። የመስቀል ደመራ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያከብር ለስድስተኛ ጊዜ ነው። አዲስ አበባን ለረጅም ጊዜ አውቃታለሁ። እንደምትመለከተኝ የሀገሩን ባህላዊ ልብስ ለብሼ አምሮብኛል፡፡ አሁን ላይ አዲስ አበባ በጣም ውብ እየሆነች ትገኛለች፡፡ እኔ እንደተገነዘብኩት የመስቀል ደመራ በዓልን የሚያከብር የሰው ብዛት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በኮቪድ ጊዜም እዚሁ ነበርኩ፡፡ በዚያን ጊዜ ጥቂት ሰው ነበር ያከበረው፡፡ ነገር ግን በዓመቱ ህዝቡ በተለመደው መሰረት ግጥም ብሎ ነበር ሲያከብር የነበረው፡፡
ማህበረሰቡ እምነቱንም ባህሉንም ይወድዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ድባብ ልዩ ነው፡፡ ታደሚዎቹ ሁሉም በባህላዊ ልብስ ተውበው ነው ወደ መስቀል አደባባይ የሚተምሙት፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ መስቀል ደመራ ያሉ ልዩ ልዩ በዓላት በአንድነት ያከብራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የበዓል አከባበር በየትኛውም የዓለም ክፍል የለም፡፡ ስለሆነም እነዚህን ግሩም የሆኑ እሴቶች በስፋት ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቅ አለባቸው፡፡
ሬና ሺማዙ
ሬና ሺማዙ ትባላለች፡፡ የመጣችው ከሩቅ ምስራቅ ጃፓን ሀገር ነው፡፡ ሀሳቧን እንደሚከተለው ተናግራለች፡፡ ወደ አፍሪካ ብሎም ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ከሀገሬ ውጭ ሌላ ሀገር ስረገጥ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ ሁለት ወራት አልፎኛል፡፡ ሕዝቡ ደስ የሚልና እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ህብረተሰቡ ኃይማኖተኛ ነው፤ ሰው አክባሪም ናቸው፡፡ በዚህ ሰዓት እዚህ ሀገር በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ህዝባዊ ትዕይንት አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በዚህ ሰዓት እዚህ በመሆኔ በጣም ዕደለኛ ነኝ፡፡ በተለይ በሴቶች አለባበስ እጅግ ተደምሜያለሁ፤ እንደዚህ ዓይነት ሁነት ቀልብ ይገዛል፡፡ እኔ ያየሁትን ይህንን ድንቅ የአደባባይ በዓል ወደ ሀገሬ ስመለስ ጓደኞቼ መጥተው እንዲታደሙ እነግራቸዋለሁ፡፡
የመስቀል ደመራ በዓልን ሳከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኃይማኖታዊ ትዕይት አይቼ አላውቅም፡፡ በጣም ደስ የሚል ድባብ አለው፡፡ የታዳሚዎች አለባበስም እጅግ በጣም ውብ ነው፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡ ለባህሉ እና ለእምነቱ ያለው አመለካከት ግሩም ነው፡፡ ይህንን ቆንጆ ባህል ተንከባክቦ ለቱሪዝም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ማኪካ ጌንችል
ማኪካ ጌንችል የሲውዲን ሀገር ዜጋ ናት። መደበኛ ስራዋ አስጎብኚነት ነው። በመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተሳትፋለች። ስራዬ አስጎብኚነት ስለሆነ እንደዚህ ዓይነት ሁነቶች ቀልቤን ይገዙኛል። በደረስኩበት ቦታ ሁሉ ምስል የመውሰድ ልምድ አለኝ፡፡ አምና በዚህ ሰዓትም እዚሁ ነበርኩ፤ ብዙ ማስታወሻ ፎቶዎች አሉኝ፡፡ ዘንድሮ ግን ልዩ ነው፡፡ ከተማዋ ተውባለች። ባለፈው ዓመት መጥቼ በማየቴ ዘንድሮም ጓደኛዬን ይዤ መጥቻለሁ፡፡
አዲስ አበባ በጣም ተለውጣለች። ቀደም ብዬ ስለመጣሁ አንዳንድ ቦታዎችን ዞር ዞር ብዬ ለማየት ምክሬያለሁ፤ ባለፈው ዓመት ካየሁት ጋር ሳነፃፅር ብዙ ልዩነቶች አሉ። መንገዶቹ ውብ ሆነዋል፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡ ህዝቡ አብሮ ይበላል፤ አብሮ ይዝናናል ደስ ይላል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን የሚመስል ወብ ባህል እያላት ለዓለም ማህበረሰብ በሚገባ አላስተዋወቀችም፡፡ እኔም ባለፈው ዓመት እንዳጋጣሚ ለስራ መጥቼ ባልመለከት አላውቀውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በየዓመቱ ከምጎበኛባቸው ሀገራት አንዷ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ጓደኞቼን ይዤ ነው የምመጣው፡፡
ራቼል ባርቴ፣ ፓተ ፓትርሴን፣ ሻር ብላየር እና ሊሳ ጂሌክ
ራቼል ባርቴ ለሁለተኛ ጊዜ፣ ፓተ ፓትርሴን ለሶስተኛ ጊዜ፣ ሊሳ ጂሌክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም ሻር ብላየር ለአምስተኛ ጊዜ መስቀል ደመራን ለመታደም በአንድነት ከአሜሪካ የመጡ ታዳሚያን ናቸው። ሁላችንም በህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በጣም ደስተኞች ነን፡፡ በተለይ የቡና አፈላል ስነ ስርዓቱ የትም ሀገር የለም፡፡ ሁላችንም ከሀገሬው ሰው ጋር ለመመሳሰል የሀገር ባህል ልብሶችን በጋራ አሰርተናል፡፡ በጣም አምሮብናል አይደል? አዲስ አበባ ከተላበሰችው ውብ ገፅታ ጋር ራሳችንን ለማቀራረብ ጥረት አድርገናል፡፡
ሻር ብላየር ከሁሉም ጓደኞቼ ቀድሜ የመስቀል ደመራን በአዲስ አበባ በማክበሬ ቀስ በቀስ ጓደኞቼን ይዤ መምጣት ጀመርኩ። አሁን አራት ደርሰናል፡፡ በቀጣይም ሌሎች ሰዎችን ጨምረን እንመጣለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት የአደባባይ ፌስቲቫሎች ብዙ ቱሪስቶችን የመሳብ አቅም አላቸው፡፡ ደመራን በደንብ ማስተዋወቅ ቢቻል ከዚህም በበለጠ እያደገና እየሰፋ የሚሄድ በዓል ነው፡፡
ቪለዳን ኤርዲን
ቪለዳን ኤርዲን የመጣችው ከቱርክዬ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ስለመስቀል ደመራ እዚያው ቱርክዬ እያለሁ ብዙ ተነግሮኛል ትላለች፡፡ እንዳጋጣሚ አንዲት ስፔናዊት ጓደኛዬ ስለ መስቀል ደመራ ብዙ አውርታኛለኝ መጥቼ እንዳየው አጓጉታኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ለመምጣት የወሰንኩት፡፡ መጥቼ በዚህ አስገራሚ በዓል ላይ መሳተፍ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
እውነት ለመናገር አዲስ አበባን ከጠበቅኩት በላይ ሆና ነው ያገኘኋት። የመስቀል ደመራ ለማክበር ብመጣም በቆይታዬ አንድነት ፓርክን ጎብኝቻለሁ፤ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው እንስሳትን እንደ አንበሳ፤ ቀጭኔና ሌሎችን ለማየት ችያለሁ። የመስቀል ደመራን ለመታደም ብመጣም በመሃል ከተማ እንደዚህ ዓይነት የአራዊት መኖሪያ መመልከት በጣም ደስ ይላል፡፡ የማህበረሰቡ ሰው አክባሪነት የተለየ ነው። ሌሎች የመዝነኛ ቦታዎችንም በቀጣይ ጊዜያት እጎበኛለሁ፡፡
በቶለሳ መብራቴ