የውጭ ምንዛሪ ልዩነትን ማጥበብ ለምን አስፈለገ?

በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ እንግሊዝ ያሉ ሀገራት ብሔራዊ ወይም ማዕከላዊ ባንኮችን መመስረት ጀመሩ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ማዕከላዊ ባንኮች የገንዘብ አቅርቦትን መቆጣጠር እና ምንዛሪዎችን የማረጋጋት ኃላፊነትን ተወጡ። ይህም የሀገርን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደመጣ ታዋቂው የምጣኔ ሀብት ምሁር ቲም ዌተርስ (ዶ/ር) “Foreign Exchange: A Practical Guide to the FX Markets” በተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፋቸው አትተዋል፡፡

ቲም ዌተርስ (ዶ/ር) በጥናታዊ መፅሐፋቸው እንደገለፁት፣ የውጭ ምንዛሪን በመግዛትና በመሸጥ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ለአብነትም የገበያ ግልጽነትን ይፈጥራል፡፡ ይሄውም ሸማቾች በግዢ እና ሽያጭ ዋጋዎች መካከል ፍትሃዊ እና ወጥ የሆነ አሰራርን ሲመለከቱ በፋይናንሺያል ተቋማት እና በአጠቃላይ ገበያ ላይ ያላቸው እምነት ከፍ ይላል።

በተጨማሪም፣ በአለም አቀፍ ንግድ እና ተወዳዳሪነት ላይ የሀገርን ከፍታ ይጨምራል፤ በባንኮች እና በፋይናንስ ተቋማት መካከል ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ያደርጋል። የተሻሉ አገልግሎቶችን እና ዋጋዎችን እንዲያቀርቡ ያበረታታል፤ ይህም ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ተለዋዋጭነትን በመቀነስ የምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋት ይረዳል። ይህ መረጋጋት በውጭ ምንዛሪ ላይ ለተመሰረቱ ንግዶች ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም ከምንዛሪ ተመን ውጣ ውረድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን እና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል። ይህም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን እና ትርፋማነትን ያሳድጋል።

የምጣኔ ሀብት ምሁር ቲም ዌተርስ (ዶ/ር) እንደሚሉት የውጭ ምንዛሪን በመግዛትና በመሸጥ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይህም በመሆኑ በአመዛኙ ባለሀብቶች ፍትሃዊ እና ግልፅ የገንዘብ አሠራሮችን የሚከተሉ ሀገራትን ይመርጣሉ፡፡

ሀገራት በውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለውን ልዩነት ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ባደረገ መልኩ ሲያስተካክሉ አሰራራቸውን ከዓለም አቀፍ ደንቦች ጋር ያጣጥማሉ፡፡ ይህም ተዓማኒነታቸውን በማጎልበት እና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲዋሃዱ ስለሚያደርጋቸው በምትኩ ብዙ ተቀባይነትን እና ተመራጭነትን ይዞላቸው ይመጣል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ሽያጭና ግዢ መካከል የጎላ ልዩነት እንዳይኖር ማሳሰቡ ውጤት ማምጣት ጀምሯል

በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ በፋይናንሺያል ገበያ ውስጥ ፍትሃዊነትን፣ መረጋጋትን እና ተወዳዳሪነትን ለማስፈን በመጨረሻም ሸማቾችን፣ በንግድ ወይም በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ዜጎችን በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ ድርሻ አለው ይላሉ ቲም ዌተርስ (ዶ/ር)።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በውጭ ምንዛሪ ሽያጭና ግዢ ላይ የጎላ ልዩነት እንዳይፈጠር የተለያዩ መቆጣጠሪያ ስልቶችን ተከትሏል። ባንኩ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃውም በውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት አሳስቧል፡፡

ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየዕለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ባንኩ  ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ መታየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ። ባንኮች በውጭ ምንዛሬ መሸጫ ዋጋቸው ላይ ካደረጉት ቅናሽ ባሻገር በመግዣ ዋጋቸውም ላይ ከ10 ብር በላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ያሰራጫቸው መረጃዎች ዋቢ ናቸው፡፡

አል-ዐይን ሚዲያ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም “በባንኮች 1 ዶላር በስንት ብር እየተመነዘረ ነው?” በሚል ርዕስ  በሰራው ዘገባ የግል ንግድ ባንኮች ለ1 ዶላር ከ117 እስከ 121 ብር መግዣ፤ ከ119 እስከ 123 ብር መሸጫ ዋጋ አውጥተዋል፡፡

እንደመረጃው ከሆነ ባንኮቹ ቀደም ሲል በመግዣና መሸጫ ዋጋቸው መካከል ሰፋ ያለ ልዩነት ነበር፡፡ ለአብነትም በመስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም የግል ንግድ ባንኮች 1 ዶላርን እስከ 112 ብር እየገዙ፤ እስከ 126 ብር ይሸጡ ነበር። በዚህም ባንኮች በየዕለቱ በሚያወጡት የውጭ ምንዛሬ የዋጋ ተመን ላይ በመግዣ እና በመሸጫው መካከል ከ10 በላይ ልዩነት ሲታይበት ቆይቷል።

ብሄራዊ ባንክ በበኩሉ ባንኮች የምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በራሳቸው እና ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ስምምነት የገበያውን ሁኔታ ግልፅና የአሰራር ሥርዓትን መሠረት ባደረገ የማስተካከል ነፃነት እንዳላቸው ጠቁሟል። ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ክፍያዎችንና ኮሚሽኖችን ለደንበኞቻቸው በተናጠል ማሳወቅ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል፡፡

ባንኮች ተወዳዳሪ ክፍያዎችን ሲያቀርቡም ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቃኘት ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል። በተጨማሪም ባንኮች የኮሚሽን ወይም ተያያዥነት ያላቸው ክፍያዎችንና ከደንበኞቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው የገንዘብ ልውውጦችን በግልጽ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ እነዚህ የክፍያ ሂደቶችም ለብሔራዊ ባንክ በተለመደው መልኩ በመደበኛነት ማሳወቅ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

ይህንን አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጀማ ሐጂ ከሳይንሱ አንፃር ማንኛውም የገበያ ዋጋ ነፃ ማድረግ የተወዳዳሪ ገበያ ባህሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የአካባቢው ሁኔታ ደግሞ ገበያው ተወዳዳሪ ሳይሆን ቀርቶ ተወዳዳሪ ላድርግ ማለት የበለጠ ይለጠጥና እንደ ሀገርም ሆነ ህዝብንም ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡

ባንኮች  ምንዛሬ  መግዣና መሸጫ  ዋጋ ከደንበኞቻው  ጋር ባላቸው  ስምምነት በገበያው  ሁኔታ ተመርተው  የሚወስኑ ቢሆንም ክትትልና  ቁጥጥር ሊለየው  አይገባም።

2 በመቶ የሚለው ጉዳይ ከተወዳዳሪ ገበያ ባህሪ ጋር ምን ያህል የሚጣጣም ነው? የሚለውና መሰል አለም አቀፍ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ የመከሩት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አሁን ባለንበት ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር ነፃ ገበያ የሚለው አስተሳሰብ እንደ አለማችንም ችግር ያመጣና አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስም እንዳስከተለ አስታውሰዋል፡፡

በተለይም ከሰው ልጅ ባህሪ በተለይም አጋጣሚውን በመጠቀም ለመበልፀግ ከመፈለግ አንፃር የሆነ ነገርን ዝም ብሎ መለጠጥ የራሱ ጉዳት ስላለው ትክክለኛ የሆነ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ ይህም በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በላከው ደብዳቤም በውጭ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ፕሮፌሰር ጀማ በማብራሪያቸው፣ እንደ ሀገር ካለው የግንዛቤ ክፍተት አንፃር በተለይም የውጭ ምንዛሪን ስርዓት ባለው መልኩ ማስኬድ በሀገር ላይ ጉልህ የሆነ ውጤት ያመጣል፡፡ ለዚህም የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል። እንደኛ ባሉ ባላደጉ ሀገራት ቀርቶ በሌሎቹም ያደጉ ሀገራት ልቅ የሆነ ነፃ ገበያ የለም። በመሆኑም መንግስት ክንዱን በጣም ሳያበዛም ሳያላላም ጣልቃ ገብቶ ነገሮችን በተወሰነ መልኩ የማስተካከል ሁኔታ አለ። በጣም በተዛባበት ቦታም የራሱን አማራጭ ለህዝብ ማቅረብ ግድ ይለዋል፡፡

በመሆኑም ብሔራዊ ባንኩ በውጭ ምንዛሬ ላይ በተጠና ሁኔታ ማስተካከያዎች ማድረጉ በየጊዜውም ሁኔታዎችን እያየ ማሻሻሉ ለሀገርም ሆነ ለህብረተሰቡ በጣም ጠቃሚ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) የውጭ ምንዛሪን አስመልክቶ ይፋ ያደረጋቸው የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እና የአለም ባንክ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት በውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫዎች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች የሸማቾችን መተማመን ከማሳደግ ባለፈ በሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስተካከል ያግዛል፡፡

እንደ መረጃዎቹ ከሆነ በርካታ ሀገራት የውጭ ምንዛሬ መሸጫና መግዣን ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር የተጣጣመ እንዲሆን ያደርጋሉ። ለምሳሌ የጃፓን ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎችን በንቃት ከሚያስተዳድሩ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ ላይ ተከታታይነት ያላቸው ማስተካከያና ቁጥጥሮችን ያደርጋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በገበያው ውስጥ ጣልቃ በመግባት በውጭ ምንዛሬ ዋጋ ላይ  መረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሰራርም በሀገሪቱ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እያስቻለ ስለመሆኑም በመረጃዎቹ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩልም የአውስትራሊያ መንግስት ተወዳዳሪ የገንዘብ ልውውጥ ልምዶችን በሚገባ ተግባራዊ ለማድረግ በውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ ላይ ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ይጠቀሳል፡፡ ይህም በግዢ እና ሽያጭ ዋጋዎች መካከል በአንፃራዊነት ጠባብ ስርጭት እንዲኖር አድርጓል፤ ይህም የሸማቾችን የውጭ ምንዛሪ ተሳትፎ አበረታቷል። ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ ላይ ወጥ፣ ግልፅና አዋጭ አሰራርን በመከተሏ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ ከንግድ አጋሮቿ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር  አጠናክራበታለች።

ጤናማ፣ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የፋይናንስ ስርዓት ለመፍጠር የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ መካከል ያለውን ልዩነት መቀነስ ወሳኝ ነው። እንደ አውሮፓ ህብረት፣ ጃፓን እና አውስትራሊያ ያሉ ሀገራት ልምድ እና በዘርፉ ከባለሙያዎች የተገኙ ግንዛቤዎች እንደሚያሳዩት እንዲህ አይነት አሰራር የሸማቾችን መተማመን እንዲጨምር፣ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲፈጠር እና ከአለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የበለጠ እንዲጣጣም ያደርጋል። ይህ በመጨረሻ ሸማቾችን፣ ነጋዴዎችን ወይም ትልልቅ በቢዝነስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ጤናማና የተሻለ ዕድገት እንዲኖረው ያደርጋል።

ትሮይ ሴጋል “የምንዛሪ መለዋወጥና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው” በሚል ርዕስ መቀመጫውን ኒዮርክ ባደረገው አለም አቀፍ የቢዝነስ ዘገባዎችን በማሰራጨት እውቅናን ባገኘው ኢንቬስቶፔዲያ ዲጂታል ሚዲያ ላይ ባሰፈረችው ጥናታዊ ዘገባዋ እንደገለፀችው፣ ብዙ ሰዎች ለምንዛሪ ዋጋ ትኩረት አይሰጡም፡፡ በቀላሉ ሲመለከቱት እምብዛም አያስፈልጋቸውም።

ምክንያቱም አብዛኛው ሰው በዛ ያላ ጊዜውን የሚያሳልፈው የተለመደውን እና የዕለት ተዕለት ኑሮውን በማከናወን ነው፡፡ ይህ ደግሞ  በአገር ውስጥ ምንዛሪ የሚካሄድ ነው። የምንዛሪ ዋጋዎች ትኩረት የሚሰጡት አልፎ አልፎ ለሚደረጉ ግብይቶች ማለትም እንደ የውጭ አገር ጉዞ፣ ከውጭ ልዩ ልዩ ምርቶችን የማስመጫ ክፍያዎች ወይም የባህር ማዶ ሐዋላዎች ላይ ነው።

ይሁን እንጂ የምንዛሬ መዋዠቅ ግን በሀገር በኢኮኖሚ ላይ ሰፊ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። ይህም ብዙሃኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች የሚነካበት አጋጣሚ አለ፡፡ የምንዛሪ ተመኖች በንግድ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በካፒታል ፍሰቶች፣ በዋጋ ግሽበት፣ በወለድ ተመኖች እና ከዚያም በላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ገልፃለች፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሀገራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም አለም አቀፍ አሰራሮችን መሰረት ባደረገ መልኩ የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከ2 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ማሳሰቡ በበጎ ጎኑ የሚታይ መሆኑን አለም አቀፍ አሰራሮችና እውነታዎች ያመላክታሉ፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review